መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 22
22
ነቢዩ ሚክያስ ንጉሥ አክዓብን እንዳስጠነቀቀው
(2ዜ.መ. 18፥2-27)
1በሰማርያም ሦስት ዓመት ተቀመጠ፤ በሶርያና በእስራኤልም መካከል ጦርነት አልነበረም። 2ከዚህም በኋላ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ። 3የእስራኤልም ንጉሥ አገልጋዮቹን፥ “ሬማት ዘገለዓድ የእኛ እንደ ሆነች፥ እኛም ከሶርያ ንጉሥ እጅ ሳንወስዳት ዝም እንዳልን ታውቃላችሁን?” አላቸው። 4የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን፥ “በሬማት ዘገለዓድ እንዋጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ትዘምታለህን?” አለው። ኢዮሣፍጥም ለእስራእል ንጉሥ፥ “እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለው።
5የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፥ “ወደ እግዚአብሔር ዛሬ ጠይቁልን” አለው። 6የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቱን አራት መቶ የሚያህሉትን ሰዎች ሰበሰበ፤ የእስራኤል ንጉሥም፥ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፥ “እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። 7ኢዮሳፍጥም፥ “የእስራኤልን ንጉሥ የእግዚአብሔርን ቃል እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን?” አለው። 8የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የይምላ ልጅ ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ” አለው። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም፥ “ንጉሥ እንዲህ አይበል” አለ። 9የእስራኤልም ንጉሥ አንዱን ጃንደረባ ጠርቶ፥ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ ጥራው” አለው። 10የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም ከጦር መሣሪያቸው ጋር በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ተናገሩ። 11የከሓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ትወጋቸዋለህ” አለ። 12ነቢያትም ሁሉ እንዲህ ብለው ትንቢት ተናገሩ፥ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ዝመት፤ እግዚአብሔርም ይረዳሃል። ሶርያውያንንና ንጉሣቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል።”
13ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ፥ “እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ” አለው። 14ሚክያስም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ” አለ። 15ወደ ንጉሡም ደረሰ። ንጉሡም፥ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር?” አለው። እርሱም፥ “ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” ብሎ መለሰለት። 16ንጉሡም፥ “በእግዚአብሔር ስም እውነት ትነግረኝ ዘንድ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። 17እርሱም አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም አለ፦ እግዚአብሔር የእነዚህ አምላክ አይደለምን? እያንዳንዱ በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ።” 18የእስራኤልም ንጉሥ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥን፥ “ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁምን?” አለው። 19ሚክያስም አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሰማሁት እኔ አይደለሁምን? እንዲህ አይደለም፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። 20እግዚአብሔርም፦ ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው? አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ ያለ ነገር ተናገረ። 21መንፈስም ወጣ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ፦ እኔ አስተዋለሁ አለ። 22እግዚአብሔርም፦ በምን ታስተዋለህ? አለው፤ እርሱም ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም፦ ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፤ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፤ እንዲሁም አድርግ አለ። 23አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።”
24የከሓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና፥ “ምን ዓይነት የእግዚአብሔር መንፈስ ነው የተናገረህ?” አለው። 25ሚክያስም፥ “እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ ውስጠኛው እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ” አለ። 26የእስራኤልም ንጉሥ፥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማዪቱም ሹም ወደ አሞን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኤሚር” ይላል። ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ፦ 27ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉአቸው” አለ። 28ሚክያስም፥ “በሰላም ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም” አለ። ደግሞም አሕዛብ ሁሉ ሆይ! ስሙኝ” አለ።#“ደግሞም አሕዛብ ሁሉ ሆይ ስሙኝ አለ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
የንጉሥ አክዓብ ሞት
(2ዜ.መ. 18፥28-34)
29የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ዘመቱ። 30የእስራኤልም ንጉሥ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን የእኔን ልብስ ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ወደ ሰልፍ ገባ። 31የሶርያም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሰረገሎች አለቆች፥ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፥ ታናሽ ቢሆን ወይም ታላቅ ከማናቸውም ጋር አትዋጉ” ብሎ አዝዞ ነበር። 32የሰረገሎች አለቆችም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፥ “በእውነት የእስራኤልን ንጉሥ ይመስላል፤” አሉ ይዋጉትም ዘንድ ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ። 33የሰረገሎች አለቆችም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። 34አንድ ሰውም ቀስቱን ድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በሳንባውና በደረቱ መካከል ወጋው፤ ሰረገለኛውንም፥ “መልሰህ ንዳ፤ ተወግቻለሁና ከሰልፍ ውስጥ አውጣኝ” አለው። 35በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ ንጉሡም ከጥዋት እስከ ማታ በሶርያውያን ፊት በሰረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ የቍስሉም ደም በሰረገላው ውስጥ ፈሰሰ፤ ማታም ሞተ። 36ፀሐይም በገባች ጊዜ አዋጅ ነጋሪው ወጥቶ፥ “ንጉሡ ሞቶአልና እያንዳንዱ ወደ ከተማው፥ እያንዳንዱም ወደ ሀገሩ ይሂድ” ብሎ አዋጅ ነገረ።
37ወደ ሰማርያም መጡ፤ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት፤ 38ሰረገላውንም በሰማርያ ምንጭ አጠቡት። እግዚአብሔርም በነቢዩ አድሮ እንደ ተናገረ ውሾችና ጅቦች ደሙን ላሱት። አመንዝሮች ሴቶችም በደሙ ታጠቡበት። 39የቀረውም የአክዓብ ነገር፥ ያደረገውም ነገር ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የሠራው ቤት፥ የሠራቸውም ከተሞች ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 40አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
ስለ ይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ
(2ዜ.መ. 20፥31—21፥1)
41የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ። 42ኢዮሣፍጥም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ አምስት ዓመት ጎበዝ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ አምስት ዓመት ነገሠ። እናቱም ዓዙባ የተባለች የሴሜይ ልጅ ነበረች። 43በአባቱም በአሳ መንገድ ሁሉ ሄደ፤ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን አደረገ፤ ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉትን መስገጃዎችን አላራቀም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። 44ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ታረቀ።
45የቀረውም የኢዮሣፍጥ ነገር፥ ኀይሉም፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 46ከአባቱም ከአሳ ዘመን የቀረውን ርኩስ ሥራ ከምድር አጠፋ። 47በኤዶምያስም ንጉሥ አልነበረም፤ ሹሙም እንደ ንጉሥ ነበረ። 48ኢዮሣፍጥም ወደ ኦፌር ሄደው ወርቅ ያመጡ ዘንድ በተርሴስ መርከብን ሠራ፤ ነገር ግን መርከቢቱ በጋሴዎንጋቤር ተሰብራለችና አልሄደችም። 49የአክዓብም ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን፥ “አገልጋዮችህ ከአገልጋዮቼ ጋር በመርከብ ይሂዱ” አለው፤ ኢዮሣፍጥ ግን አልወደደም። 50ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮራም ነገሠ።#ምዕ. 22 ከቍ. 47 እስከ 50 ያለው በግሪኩ የለም።
51በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመተ መንግሥት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። 52በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ በአባቱ በአክዓብ፥ በእናቱም በኤልዛቤል መንገድ፥ እስራኤልንም ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሄደ። 53በዓሊምንም አመለከ፤ ሰገደላቸውም፤ ከእርሱም አስቀድሞ አባቶቹ እንዳደረጉት ሁሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 22: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ