መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 20
20
(በዕብ. ምዕ. 21 ነው።)
የናቡቴ በግፍ መገደል
1ለኢይዝራኤላዊው ለናቡቴ በሰማርያ ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን ቦታ ነበረው። 2አክዓብም ናቡቴን፥ “በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ቦታ አደርገው ዘንድ የወይን ቦታህን ስጠኝ፤ ስለ እርሱም ከእርሱ የተሻለ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ወይም ብትወድድ ዋጋውን ወርቅ እሰጥሃለሁ” ብሎ ተናገረው። 3ናቡቴም አክዓብን፥ “የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር አያምጣብኝ” አለው። 4አክዓብም አዝኖ ሄደ፤ በአልጋውም ላይ ተኝቶ ፊቱን ተሸፋፈነ፤ እንጀራንም አልበላም።
5ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ ገብታ፥ “ምን ያሳዝንሃል? እንጀራስ የማትበላ ምን ሆነሃል?” አለችው። 6እርሱም፥ “ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን፦ የወይንህን ቦታ በገንዘብ ስጠኝ፤ ወይም ብትወድድ በፋንታው ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ ብዬ ተናገርሁት፤ እርሱ ግን የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም ስለ አለኝ ነው” አላት። 7ሚስቱ ኤልዛቤልም፥ “አሁንም አንተ የእስራኤል ንጉሥ ሆነህ እንደዚህ ታደርጋለህን? ተነሣ፤ እንጀራንም ብላ፤ ራስህንም አጽና፤ ልብህም ደስ ይበላት፤ የኢይዝራኤላዊውንም የናቡቴን የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ” አለችው። 8በአክዓብም ስም ደብዳቤ ጻፈች፤ በማኅተሙም አተመችው፤ በከተማው ወደ ነበሩትና ከናቡቴም ጋር ወደ ተቀመጡት ሽማግሌዎችና አለቆች ደብዳቤውን ላከች። 9የዚያች ደብዳቤም ቃል እንዲህ ይላል፥ “ጾምን ጹሙ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ መካከል በከፍተኛ ቦታ አስቀምጡት፤ 10ሁለት የሐሰት ምስክሮችንም በፊቱ አስቀምጡና፦ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው ይመስክሩበት፤ አውጥታችሁም እስኪሞት ድረስ በድንጋይ መትታችሁ ግደሉት።”
11በከተማውም የተቀመጡት የከተማው ሰዎችና ሽማግሌዎች፥ አለቆችም ኤልዛቤል እንዳዘዘቻቸውና ወደ እነርሱ በተላከው ደብዳቤ እንደ ተጻፈው እንዲሁ አደረጉ። 12የጾም አዋጅም ነገሩ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት በከፍተኛ ቦታ አስቀመጡት። 13ሁለቱም የዐመፅ ልጆች የሆኑ ሰዎች ገብተው በፊቱ ቆሙ፤ “እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድበሃል” ብለው መሰከሩበት። የዚያ ጊዜም ከከተማ አውጥተው በድንጋይ ደብድበው ገደሉት። 14ወደ ኤልዛቤልም፥ “ናቡቴ በድንጋይ ተደብድቦ ሞተ” ብለው ላኩ። 15ኤልዛቤልም በሰማች ጊዜ አክዓብን፥ “ናቡቴ ሞቶአል እንጂ በሕይወት አይደለምና በገንዘብ ይሰጥህ ዘንድ እንቢ ያለውን የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ ተነሥተህ ውረስ” አለችው። 16አክዓብም ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ልብሱን ቀደደ ፤ ማቅንም ለበሰ” የሚል ይጨምራል። ወደ ኢይዝራኤላዊው ወደ ናቡቴ ወይን ቦታ ሊወርሰው ተነሥቶ ወረደ።
17እግዚአብሔርም ቴስብያዊው ኤልያስን እንዲህ አለው፦ 18“ተነሥተህ በሰማርያ የሚኖረውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ እነሆ፥ ይወርሰው ዘንድ በወረደበት በናቡቴ የወይን ቦታ ውስጥ አለ። 19እንዲህም ብለህ ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ናቡቴን ገድለህ ወረስኸው፤ ስለዚህም ደግሞ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጅቦችና ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል፤ አመንዝራዎችም በደምህ ይታጠባሉ” ብለህ ንገረው። 20አክዓብም ኤልያስን፥ “ጠላቴ ሆይ! አገኘኸኝን?” አለው። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት፥ “አግኝቼሃለሁ፤ ታስቈጣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገሃልና እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 21እነሆ፥ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፤ እሳትን ከኋላህ አነድዳለሁ፤ ዐጥር ተጠግቶ እስከሚሸን ድረስ የአክዓብን ዘር አጠፋዋለሁ፤ በእስራኤል ውስጥ ያሉትንም፥ የሌሉትንም እነቅላለሁ፤ 22በሥራህም አስቈጥተኸኛልና፥ እስራኤልንም አስተሃልና ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።” 23እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረ፥ “በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ኤልዛቤልን ውሾች ይበሉአታል፥ 24ከአክዓብም ወገን በከተማዪቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።” 25ነገር ግን አክዓብ በእግዚአብሔር ፊት ክፉን ያደርግ ዘንድ ራሱን ሸጠ፤ ሚስቱ ኤልዛቤል አስታዋለችና። 26እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ያጠፋቸው አሞራውያን እንደ ሠሩት ሁሉ፥ ጣዖትን በመከተል እጅግ ርኩስ ነገርን ሠራ።
27አክዓብም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ደነገጠ፤ ልብሱንም ቀደደ፤ እያለቀሰም ሄደ፤ በሰውነቱም ላይ ማቅ ለበሰ፤ ጾመም፤ ኢይዝራኤላዊው ናቡቴንም በገደለበት ቀን ደግሞ ማቅ ለብሶ ነበር። 28የእግዚአብሔርም ቃል ስለ አክዓብ ወደ ባሪያው ወደ ኤልያስ መጣ፤ እግዚአብሔርም አለው፦ 29“አክዓብ በፊቴ እንደ ደነገጠ አየህን? በፊቴ በልጁ ዘመን በቤቱ ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ እንጂ በእርሱ ዘመን ክፉ ነገር አላመጣም።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 20: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ