መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 22
22
ቤተ መቅደስን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት
1ዳዊትም፥ “ይህ የአምላኬ የእግዚአብሔር ቤት ነው፤ ይህም ለእስራኤል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ ነው” አለ። 2ዳዊትም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ይሰበስቡ ዘንድ አዘዘ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ለመሥራት የሚወቀሩትን ድንጋዮች ይወቅሩ ዘንድ ጠራቢዎችን አኖረ። 3ዳዊትም ለበሮቹ ሳንቃ ለሚሆኑ ለምስማርና ለመጠረቂያ ብዙ ብረት፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይመዘን ናስ አዘጋጀ። 4ሲዶናውያንና የጢሮስ ሰዎችም ብዙ የዝግባ እንጨት ለዳዊት ያመጡ ነበርና ቍጥር የሌላቸውን የዝግባ እንጨቶች አዘጋጀ። 5ዳዊትም፥ “ልጄ ሰሎሞን ታናሽና ለጋ ብላቴና ነው፤ ለእግዚአብሔርም የሚሠራው ቤት እጅግ ማለፊያና በሀገሩ ሁሉ ስሙና ክብሩ እንዲጠራ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ስለዚህ አዘጋጅለታለሁ” አለ። ዳዊትም ሳይሞት አስቀድሞ ብዙ አዘጋጀ።
6ልጁንም ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ አዘዘው። 7ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፥ “ልጄ ሆይ፥ እኔ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ በልቤ አስቤ ነበር። 8ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ እጅግ ብዙ ደም አፍስሰሃል፤ ታላቅም ሰልፍ አድርገሃል፤ በፊቴም በምድር ላይ ብዙ ደም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም። 9እነሆ፥ ልጅ ይወለድልሃል፤ የዕረፍት ሰውም ይሆናል፤ በዙሪያውም ካሉ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙ ሰሎሞን ይባላልና፥ በዘመኑም ሰላምንና ጸጥታን ለእስራኤል እሰጣለሁ። 10እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤ ልጅም ይሆነኛል፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ የመንግሥቱንም ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም አጸናለሁ። 11አሁንም ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም እንደ ተናገረው ያከናውንልህ፤ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ። 12ብቻ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ሕግ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ፤ መንግሥትህንም በእስራኤል ላይ ያጽና። 13እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ሙሴን ያዘዘውን ሥርዐትና ፍርድ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ ብትጠነቀቅ በዚያን ጊዜ ይከናወንልሃል፤ አይዞህ፥ በርታ፤ አትፍራ፤ አትደንግጥም። 14አሁንም፥ እነሆ፥ በድህነቴ ለእግዚአብሔር ቤት መቶ ሺህ መክሊት ወርቅና አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፥ ሚዛንም የሌላቸው ብዙ ናስና ብረት አዘጋጅቻለሁ፤ ደግሞም የማይቈጠር ብዙ የዝግባ እንጨትና ድንጋዮች አዘጋጅቻለሁ፤ አንተም ልጄ ከዚያ በላይ ጨምር። 15አንተም ብዙ ሠራተኞችን፥ ድንጋይና እንጨት ወቃሪዎችንና ጠራቢዎችን፥ ሥራውንም ሁሉ ለማድረግ ጠቢባን ሰዎችን አብዝተህ ጨምር። 16ቍጥር በሌለው በወርቅና ብር፥ በናስና ብረት ተነሥተህ ሥራ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን።”
17ዳዊትም ደግሞ ልጁን ሰሎሞንን ይቀበሉትና ያግዙት ዘንድ የእስራኤልን አለቆች ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ 18“አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይደለምን? በምድርም የሚቀመጡትን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ምድርም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ፊት ተገዝታለችና በዙሪያችሁ ከአሉ ጠላቶቻችሁም ሁሉ ዕረፍትን ሰጥቶአችኋል። 19አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈልጉ ዘንድ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ስጡ፤ ለእግዚአብሔርም ስም ወደሚሠራው ቤት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ታመጡ ዘንድ ተነሥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 22: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ