መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 21
21
ዳዊት የእስራኤልን ሕዝብ እንደ ቈጠረ
(2ሳሙ. 24፥1-25)
1ያንጊዜም ሰይጣን በእስራኤል ላይ ተነሣ፤ እስራኤልንም ይቈጥር ዘንድ ዳዊትን አነሣሣው። 2ዳዊትም ኢዮአብንና የሕዝቡን አለቆች ሁሉ፥ “ሂዱ፥ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ እስራኤልን ቍጠሩ፤ ድምራቸውንም አውቅ ዘንድ አስታውቁኝ” አላቸው። 3ኢዮአብም፥ “እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አሁን ባለበት መቶ እጥፍ ይጨምር፤ የጌታዬ የንጉሥ ዐይኖችም ይዩ፤ ሁሉም የጌታዬ አገልጋዮች ናቸው፤ በእስራኤል ላይ በደል ይሆን ዘንድ ይህን ነገር ጌታዬ ለምን ይሻል?” አለ። 4ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብ ላይ አሸነፈ፤ ኢዮአብም ወጥቶ በእስራኤል ሁሉ ላይ ተዘዋወረ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ። 5ኢዮአብም የቈጠራቸውን የሕዝቡን ድምር ለዳዊት ሰጠ፤ ከእስራኤልም ሁሉ አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ተገኙ፤ ከይሁዳም አራት መቶ ሰባ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ተገኙ። 6የንጉሡ ትእዛዝ ግን በኢዮአብ ዘንድ የተጠላ ነበረና ሌዊና ብንያም ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም።
7ይህም ነገር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ፤ በእስራኤልም ላይ መቅሠፍትን አመጣ። 8ዳዊትም እግዚአብሔርን፥ “ይህን በማድረግ እጅግ በድያለሁ፤ አሁንም ታላቅ ስንፍና አድርጌአለሁና የባሪያህን ኀጢአት ታስወግድ ዘንድ እለምንሃለሁ” አለው። 9እግዚአብሔርም ለነቢዩ ለጋድ እንዲህ አለው፦ 10“ሂድ፥ ለዳዊት፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሦስቱን ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፤ አደርግብህ ዘንድ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ ብለህ ንገረው።” 11ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምትወድደውን ምረጥ። 12የሦስት ዓመት ራብ፥ ወይም ሦስት ወር የጠላቶችህ ሰይፍ እንዲያገኝህ ከጠላቶችህ መሰደድን፥ ወይም ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ፥ ቸነፈርም በምድር ላይ መሆንን፥ የእግዚአብሔርም መልአክ በእስራኤል ምድር ሁሉ ማጥፋትን ምረጥ፤ አሁንም ለላከኝ ምን እንደምመልስ አስረዳኝ” አለው። 13ዳዊትም ጋድን፥ “እነዚህ ሦስት ነገሮች እጅግ ይከብዱኛል፥ እጅግም ተጨንቄአለሁ፤ አሁንም ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ይሻለኛል፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ” አለው።
14እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቸነፈርን ሰደደ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰዎች ወደቁ። 15እግዚአብሔርም ያጠፋት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም መልአክን ሰደደ፤ ሊያጠፋትም በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር አይቶ ከመቅሠፍቱ ይቅር አለ፤ የሚያጠፋውንም መልአክ፥ “በቃህ፤ አሁን እጅህን መልስ” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር። 16ዳዊትም ዐይኖቹን አነሣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትና ሽማግሌዎቹም ማቅ ለብሰው በግንባራቸው ተደፉ። 17ዳዊትም እግዚአብሔርን፥ “ሕዝቡ ይቈጠር ዘንድ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? የበደልሁና ክፉ የሠራሁ እኔ ነኝ፤ እነዚህ በጎች ግን ምን አድርገዋል? አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን፤ ነገር ግን አቤቱ በሕዝብህ ላይ ለጥፋት አትሁን” አለው።
18የእግዚአብሔርም መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ ለዳዊት እንዲነግረው ጋድን አዘዘው። 19ዳዊትም በእግዚአብሔር ስም እንደ ተናገረው እንደ ጋድ ነገር ወጣ። 20ኦርናም ዘወር ብሎ ንጉሡ ዳዊትን፥#ዕብ. “መልአኩን” ይላል። ከእርሱም ጋር ተሸሽገው የነበሩ አራቱን ብላቴኖቹን አየ። ኦርናም ስንዴ ያበራይ ነበር። 21ዳዊትም ወደ ኦርና መጣ፤ ኦርናም ከአውድማው ወጥቶ ዳዊትን ተቀበለው። በምድርም ላይ ወድቆ ሰገደለት። 22ዳዊትም ኦርናን፥ “በላዩ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እሠራ ዘንድ ይህን የአውድማ ስፍራ ስጠኝ፤ በሙሉ ዋጋ ሽጥልኝ፤ መቅሠፍቱም ከሕዝቤ ይከለከላል” አለው። 23ኦርናም ዳዊትን፥ “ለአንተ ውሰደው፤ ጌታዬ ንጉሡም በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ያድርግ፤ እነሆ፥ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሬዎቹን፥ ለእንጨትም የአውድማውን ዕቃ፥ ለእህልም ቍርባን ስንዴውን እሰጥሀለሁ፥ ሁሉን እሰጣለሁ” አለው። 24ንጉሡም ዳዊት ኦርናን፥ “አይደለም፥ ነገር ግን ለአንተ ያለውን ለእግዚአብሔር አምጥቼ የሚቃጠል መሥዋዕት በከንቱ አላቀርብምና በተገቢው ዋጋ እገዛዋለሁ” አለው። 25ዳዊትም ስለ ስፍራው ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ በሚዛን ለኦርና ሰጠው። 26ዳዊትም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱንም መሥዋዕት አቀረበ፤ እግዚአብሔርንም ጠራ፤ ከሰማይም ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ በእሳት መለሰለት፤ እሳቱም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በላ። 27እግዚአብሔርም መልአኩን አዘዘው፤ ሰይፉንም በአፎቱ ከተተው።
28በዚያም ጊዜ እግዚአብሔር በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ እንደ ሰማው ዳዊት ባየ ጊዜ፥ በዚያ መሥዋዕትን ሠዋ። 29ሙሴም በምድረ በዳ የሠራት የእግዚአብሔር ማደሪያና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ በዚያን ጊዜ በገባዖን ባለው በኮረብታው መስገጃ ነበሩ። 30ዳዊት ግን ከእግዚአብሔር መልአክ ሰይፍ የተነሣ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደዚያ ይሄድ ዘንድ አልቻለም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 21: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ