መጽ​ሐፈ ዜና መዋ​ዕል ቀዳ​ማዊ 19

19
ዳዊት አሞ​ና​ው​ያ​ን​ንና ሶር​ያ​ው​ያ​ንን ድል እንደ አደ​ረገ
(2ሳሙ. 10፥1-19)
1ከዚ​ህም በኋላ እን​ዲህ ሆነ፤ የአ​ሞን ልጆች ንጉሥ ናዖስ ሞተ፤ ልጁም በእ​ርሱ ፋንታ ነገሠ። 2ዳዊ​ትም፥ “አባቱ ስላ​ደ​ረ​ገ​ልኝ ወረታ እኔ ለና​ዖስ ልጅ ለሐ​ናን ቸር​ነት አደ​ር​ጋ​ለሁ” አለ። ዳዊ​ትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያ​ጽ​ና​ናው መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላከ፤ የዳ​ዊ​ትም አገ​ል​ጋ​ዮች ሊያ​ጽ​ና​ኑት ወደ ሐናን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ። 3የአ​ሞን ልጆች አለ​ቆች ግን ሐና​ንን፥ “ዳዊት የሚ​ያ​ጽ​ና​ኑ​ህን ወደ አንተ የላከ አባ​ት​ህን በማ​ክ​በር ነውን? አገ​ል​ጋ​ዮ​ቹስ ከተ​ማ​ዪ​ቱን ለመ​መ​ር​መ​ርና ሀገ​ሪ​ቱ​ንም ለመ​ሰ​ለል ወደ አንተ የመጡ አይ​ደ​ሉ​ምን?” አሉት። 4ሐና​ንም የዳ​ዊ​ትን አገ​ል​ጋ​ዮች ወስዶ የጢ​ማ​ቸ​ውን ግማሽ አስ​ላ​ጫ​ቸው፤ ልብ​ሳ​ቸ​ው​ንም እስከ ወገ​ባ​ቸው ድረስ ለሁ​ለት ቀድዶ ሰደ​ዳ​ቸው። 5ሰዎ​ችም ሄደው በሰ​ዎቹ ላይ የተ​ደ​ረ​ገ​ውን ለዳ​ዊት አስ​ታ​ወ​ቁት። ሰዎ​ቹም በብዙ አፍ​ረ​ዋ​ልና ይቀ​በ​ሏ​ቸው ዘንድ ሰዎ​ችን ላኩ፤ ንጉ​ሡም፥ “ጢማ​ችሁ እስ​ኪ​ያ​ድግ ድረስ በኢ​ያ​ሪኮ ተቀ​መጡ፥ ከዚ​ያም በኋላ ተመ​ለሱ” አለ።
6የአ​ሞ​ንም ልጆች የዳ​ዊት ሰዎች እን​ዳ​ፈሩ ባዩ ጊዜ ሐናን የአ​ሞን ልጆች ንጉሥ ከሶ​ርያ መስ​ጴ​ጦ​ምያ፥ ከሶ​ርያ ሞዓካ፥ ከሱ​ባም ሰረ​ገ​ሎ​ች​ንና ፈረ​ሰ​ኞ​ችን ይቀ​ጥሩ ዘንድ አንድ ሺህ መክ​ሊት ብር ላከ። 7ሠላሳ ሁለ​ትም ሺህ ሰረ​ገ​ሎ​ችን የሞ​ዓ​ካን ንጉ​ሥና ሕዝ​ቡ​ንም ቀጠሩ፤ መጥ​ተ​ውም በሜ​ድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአ​ሞ​ንም ልጆች ከየ​ከ​ተ​ሞ​ቻ​ቸው ተሰ​ብ​ስ​በው ወደ ሰልፍ መጡ። 8ዳዊ​ትም ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮ​አ​ብ​ንና የኀ​ያ​ላ​ኑን ሠራ​ዊት ሁሉ ላከ። 9የአ​ሞ​ንም ልጆች ወጥ​ተው በከ​ተ​ማ​ዪቱ በር አጠ​ገብ ተሰ​ለፉ፤ የመ​ጡ​ትም ነገ​ሥ​ታት ለብ​ቻ​ቸው በሜ​ዳው ላይ ሰፈሩ።
10ኢዮ​አ​ብም በፊ​ቱና በኋ​ላው ሰልፍ እንደ ከበ​በው ባየ ጊዜ ከእ​ስ​ራ​ኤል ጐል​ማ​ሶ​ችን መረጠ፤ እነ​ር​ሱም ከሶ​ር​ያ​ው​ያን ጋር ተዋጉ። 11የቀ​ረ​ው​ንም ሕዝብ ለወ​ን​ድሙ ለአ​ቢሳ ሰጠው፤ እነ​ር​ሱም በአ​ሞን ልጆች ላይ ተሰ​ለፉ። 12ኢዮ​አ​ብም፥ “ሶር​ያ​ው​ያን ቢበ​ረ​ቱ​ብኝ ርዳኝ፤ የአ​ሞ​ንም ልጆች ቢበ​ረ​ቱ​ብህ እረ​ዳ​ሃ​ለሁ። 13አይ​ዞህ፥ በርታ፤ ስለ ሕዝ​ባ​ች​ንና ስለ አም​ላ​ካ​ች​ንም ከተ​ሞች እን​በ​ርታ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በፊቱ ደስ ያሰ​ኘ​ውን ያድ​ርግ” አለ። 14ኢዮ​አ​ብና ከእ​ር​ሱም ጋር የነ​በ​ረው ሕዝብ ከሶ​ር​ያ​ው​ያን ጋር ተዋጉ፤ እነ​ር​ሱም ከፊ​ታ​ቸው ሸሹ። 15የአ​ሞ​ንም ልጆች ሶር​ያ​ው​ያን ከኢ​ዮአብ ፊት እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነ​ርሱ ደግሞ ከወ​ን​ድሙ ከአ​ቢሳ ፊት ሸሹ፤ ወደ ከተ​ማ​ዪ​ቱም ገቡ። ኢዮ​አ​ብም ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም መጣ።
16ሶር​ያ​ው​ያ​ንም እስ​ራ​ኤል ድል እን​ዳ​ደ​ረ​ጓ​ቸው ባዩ ጊዜ መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ልከው በወ​ንዝ ማዶ የነ​በ​ሩ​ትን ሶር​ያ​ው​ያን አስ​መጡ፤ የአ​ድ​ር​አ​ዛ​ርም ሠራ​ዊት አለቃ ሶፋክ በፊ​ታ​ቸው ነበረ። 17ዳዊ​ትም በተ​ነ​ገ​ረው ጊዜ እስ​ራ​ኤ​ልን ሁሉ ሰበ​ሰበ፤ ዮር​ዳ​ኖ​ስ​ንም ተሻ​ግሮ መጣ​ባ​ቸው፥ ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊ​ትም ከሶ​ር​ያ​ው​ያን ጋር ተዋጋ፥ እነ​ር​ሱም ከእ​ርሱ ጋር ተዋጉ። 18ሶር​ያ​ው​ያ​ንም ከዳ​ዊት ፊት ሸሹ፤ ዳዊ​ትም ከሶ​ር​ያ​ው​ያን ሰባት ሺህ ሰረ​ገ​ለ​ኞ​ችን፥ አርባ ሺህም እግ​ረ​ኞ​ችን ገደለ፥ የሠ​ራ​ዊ​ቱ​ንም አለቃ ሶፋ​ክን ገደለ። 19የአ​ድ​ር​አ​ዛ​ርም አገ​ል​ጋ​ዮች በእ​ስ​ራ​ኤል ፊት እንደ ተሸ​ነፉ ባዩ ጊዜ ከዳ​ዊት ጋር ታረቁ፤ ተገ​ዙ​ለ​ትም፤ ሶር​ያ​ው​ያ​ንም ከዚያ ወዲያ የአ​ሞ​ንን ልጆች ይረዱ ዘንድ እንቢ አሉ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ