መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 18
18
ዳዊት በፍልስጥኤማውያን ላይ የተቀዳጀው ድል
(2ሳሙ. 8፥1-18)
1ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፤ አዋረዳቸውም፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ጌትንና መንደሮችዋን ወሰደ። 2ሞዓብንም መታ፤ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት።
3ዳዊትም በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛቱን ለማጽናት በሄደ ጊዜ ሔማታዊውን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን መታ። 4ዳዊትም ከእርሱ አንድ ሺህ ሰረገሎች፥ ሰባት ሺህም ፈረሰኞች፥ ሃያ ሺህም እግረኞች ወሰደ፤ ዳዊትም ለመቶ ሰረገሎች የሚሆኑትን ብቻ አስቀርቶ የሰረገሎቹን ፈረሶች ቋንጃ ቈረጠ።
5ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደለ። 6ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ ጭፍሮችን አኖረ፤ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ያድነው ነበር። 7ዳዊትም ለአድርአዛር አገልጋዮች የነበሩትን የወርቅ ማርዳዎች ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞአቸው መጣ። 8ከሚጢብሐትና ከተመረጡት ከአድርአዛር ከተሞች#ዕብ. “ከአድርአዛር ከተሞች ከሚጥብሐትና ኮን” ይላል። ዳዊት እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ከዚህም ሰሎሞን የናሱን ኩሬና ዓምዶች የናሱንም ዕቃ ሠራ።
9የኤማትም ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን፥ ጭፍራውንም ሁሉ እንደ መታ ሰማ። 10ቶዑም ከአድርአዛር ጋር ሁልጊዜ ይዋጋ ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ወግቶ ስለ መታው ደኅንነቱን ይጠይቀውና ይመርቀው ዘንድ ልጁን አዶራምን ወደ ዳዊት ላከው፤ ከእርሱም ጋር የወርቅና የብር፥ የናስም ዕቃ ነበረ። 11ንጉሡም ዳዊት ከአሕዛብ ሁሉ ከኤዶምና ከሞዓብ፥ ከአሞንም ልጆች፥ ከፍልስጥኤማውያንም፥ ከአማሌቅም ከማረከው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ደግሞ ለእግዚአብሔር ቀደሰ።
12ደግሞ የሶርህያ ልጅ አቢሳ ከኤዶማውያን በጨው ሸለቆ#ግእዙ “ፈለገ አግሪም ወይም አግራን” ይላል። ውስጥ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደለ። 13በዚያም ሸለቆ ምሽግ ሠርቶ#ዕብ. “በኤዶምያስ” ይላል። ጭፍሮችን አኖረ፥ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ያድነው ነበር።
14ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍርድንና ጽድቅን አደረገላቸው። 15የሶርህያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ የአሔሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሓፊ ነበረ። 16የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አቤሜሌክ ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ጸሓፊ ነበረ። 17የዮዳሄ ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ሹም ነበረ፤ የዳዊትም ልጆች በንጉሡ አጠገብ አለቆች ነበሩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 18: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ