መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 19
19
ዳዊት አሞናውያንንና ሶርያውያንን ድል እንደ አደረገ
(2ሳሙ. 10፥1-19)
1ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የአሞን ልጆች ንጉሥ ናዖስ ሞተ፤ ልጁም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 2ዳዊትም፥ “አባቱ ስላደረገልኝ ወረታ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐናን ቸርነት አደርጋለሁ” አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያጽናናው መልእክተኞችን ላከ፤ የዳዊትም አገልጋዮች ሊያጽናኑት ወደ ሐናን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ። 3የአሞን ልጆች አለቆች ግን ሐናንን፥ “ዳዊት የሚያጽናኑህን ወደ አንተ የላከ አባትህን በማክበር ነውን? አገልጋዮቹስ ከተማዪቱን ለመመርመርና ሀገሪቱንም ለመሰለል ወደ አንተ የመጡ አይደሉምን?” አሉት። 4ሐናንም የዳዊትን አገልጋዮች ወስዶ የጢማቸውን ግማሽ አስላጫቸው፤ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ለሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው። 5ሰዎችም ሄደው በሰዎቹ ላይ የተደረገውን ለዳዊት አስታወቁት። ሰዎቹም በብዙ አፍረዋልና ይቀበሏቸው ዘንድ ሰዎችን ላኩ፤ ንጉሡም፥ “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ” አለ።
6የአሞንም ልጆች የዳዊት ሰዎች እንዳፈሩ ባዩ ጊዜ ሐናን የአሞን ልጆች ንጉሥ ከሶርያ መስጴጦምያ፥ ከሶርያ ሞዓካ፥ ከሱባም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ይቀጥሩ ዘንድ አንድ ሺህ መክሊት ብር ላከ። 7ሠላሳ ሁለትም ሺህ ሰረገሎችን የሞዓካን ንጉሥና ሕዝቡንም ቀጠሩ፤ መጥተውም በሜድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአሞንም ልጆች ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ወደ ሰልፍ መጡ። 8ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኀያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ። 9የአሞንም ልጆች ወጥተው በከተማዪቱ በር አጠገብ ተሰለፉ፤ የመጡትም ነገሥታት ለብቻቸው በሜዳው ላይ ሰፈሩ።
10ኢዮአብም በፊቱና በኋላው ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ጐልማሶችን መረጠ፤ እነርሱም ከሶርያውያን ጋር ተዋጉ። 11የቀረውንም ሕዝብ ለወንድሙ ለአቢሳ ሰጠው፤ እነርሱም በአሞን ልጆች ላይ ተሰለፉ። 12ኢዮአብም፥ “ሶርያውያን ቢበረቱብኝ ርዳኝ፤ የአሞንም ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ። 13አይዞህ፥ በርታ፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ደስ ያሰኘውን ያድርግ” አለ። 14ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ከሶርያውያን ጋር ተዋጉ፤ እነርሱም ከፊታቸው ሸሹ። 15የአሞንም ልጆች ሶርያውያን ከኢዮአብ ፊት እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፤ ወደ ከተማዪቱም ገቡ። ኢዮአብም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።
16ሶርያውያንም እስራኤል ድል እንዳደረጓቸው ባዩ ጊዜ መልእክተኞችን ልከው በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን አስመጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሶፋክ በፊታቸው ነበረ። 17ዳዊትም በተነገረው ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፤ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ መጣባቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ጋር ተዋጋ፥ እነርሱም ከእርሱ ጋር ተዋጉ። 18ሶርያውያንም ከዳዊት ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞችን፥ አርባ ሺህም እግረኞችን ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሶፋክን ገደለ። 19የአድርአዛርም አገልጋዮች በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ታረቁ፤ ተገዙለትም፤ ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ እንቢ አሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 19: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ