መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 13
13
የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መወሰድዋ
(2ሳሙ. 6፥1-11)
1ዳዊትም ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች፥ ከአለቆቹም ሁሉ ጋር ተማከረ። 2ዳዊትም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ፥ “መልካም መስሎ የታያችሁ እንደ ሆነ፥ አምላካችን እግዚአብሔርም ፈቅዶ እንደ ሆነ፥ በእስራኤል ሀገር ሁሉ ለቀሩት ወንድሞቻችን በከተሞቻቸውና በመሰማሪያዎቻቸው ለሚቀመጡ ካህናትና ሌዋውያን ወደ እኛ ይሰበሰቡ ዘንድ እንላክ። 3ከሳኦልም ዘመን ጀምሮ አልፈለጓትምና የአምላካችን የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኛ እንመልሳት” አላቸው። 4ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዐይን ዘንድ ቅን ነበረና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ፥ “እንዲሁ እናደርጋለን” አሉ። 5የእግዚአብሔርንም ታቦት ከቂርያትይዓሪም ያመጡ ዘንድ ዳዊት እስራኤልን ሁሉ ከግብፅ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ኤማት መግቢያ ድረስ ሰበሰበ። 6ዳዊትም፥ እስራኤልም ሁሉ በኪሩቤል ላይ የተቀመጠውን፥ ስሙም በእርስዋ የተጠራባትን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያወጡ ዘንድ በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓሪም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ወደ ዳዊት ከተማ” ይላል። ሄዱ። 7የእግዚአብሔርንም ታቦት ከአሚናዳብ ቤት በተገኘ በአዲስ ሰረገላ ላይ አኖሩአት። ዖዛና ወንድሞቹም ሰረገላውን ይነዱ ነበር። 8ዳዊትና እስራኤል ሁሉ ከመዘምራን ጋር በበገና፥ በመሰንቆና በከበሮ፥ በጸናጽልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኀይላቸው ይዘምሩ ነበር።
9ወደ አውድማ ዳርም በደረሱ ጊዜ ላሞቹ ሰረገላውን ሲስቡ የእግዚአብሔር ታቦት ዘንበል ብላለችና ታቦቷን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ። 10እግዚአብሔርም በዖዛ ላይ ተቈጣ። እጁንም ወደ እግዚአብሔር ታቦት ስለ ዘረጋ ቀሠፈው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ። 11እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ሰበረው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም “የዖዛ ስብራት” ብሎ ጠራው። 12በዚያም ቀን ዳዊት፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ?” ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ።
13ዳዊትም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ጌት ሰው ወደ አቢዳራ ቤት አሳለፋት እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣትም። 14የእግዚአብሔርም ታቦት በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠች፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤተ ሰቡን ሁሉ ባረከ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 13: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ