መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 12
12
ከብንያም ነገድ ዳዊትን የተከተሉት
1በሴቅላቅም ከቂስ ልጅ ከሳኦል በተሸሸገ ጊዜ ወደ ዳዊት የመጡ እነዚህ ናቸው፤ በጦርነትም ባገዙት ኀያላን መካከል ነበሩ። 2ቀስተኞችም ነበሩ፤ በቀኝና በግራም እጃቸው ድንጋይ ሊወነጭፉ፥ ፍላጻም ሊወረውሩ ይችሉ ነበር፤ ከብንያም ወገን የሳኦል ወንድሞች ነበሩ። 3አለቃቸውም አኬዘር ነበረ፤ የጊብዓዊው የሰማዓ ልጅ ኢዮአስ፥ የዓዝሞት ልጆች ኢዮኤልና ፋሌጥ፥ በራኪያና ዓናቶታዊው ኢዩ፤ 4ገባዖናዊው ሰማያስ፥ እርሱ በሠላሳው መካከልና በሠላሳው ላይ ኀያል ሰው ነበረ፤ ኤርምያስ፥ ሕዝኤል፥ ዮሐናን፥ ገድሮታዊ ዮዛባት፤ 5ኤልዮዝ፥ ኢያሪሙት፥ በዓልያ፥ ሰማራያ፥ ሐሩፋዊው ሰፋጥያስ፤ 6ቆሬያውያን ሕልቃና፥ ኢሰያ፥ ዓዘርኤል፥ ዮዛር፥ ይሰከአም። 7የግዶር ሰው የይሮሐም ልጆች ዮዔላ፥ ዝባድያ።
ከጋድ ወገን ዳዊትን የተከተሉ
8ዳዊትም በምድረ በዳ ውስጥ ባለችው በአንባዪቱ ሳለ ከጋድ ወገን የሆኑ እነዚህ ጋሻና ጦር የሚይዙ፥ ጽኑዓን፥ ኀያላን ሰልፈኞች፥ ወደ እርሱ ተጠጉ፤ ፊታቸውም እንደ አንበሳ ፊት ነበረ፤ በተራራም ላይ እንደሚዘልል ሚዳቋ ፈጣኖች ነበሩ። 9አለቃው አዝር፥ ሁለተኛው አብድያ፥ ሦስተኛው ኤልያብ፤ 10አራተኛው መስመና፥ አምስተኛው ኤርምያስ፥ 11ስድስተኛው ኤቲ፥ ሰባተኛው ኤሊኤል፥#ግሪክኛው “ኤልያብ” ይለዋል። 12ስምንተኛው ዮሐናን፥ ዘጠነኛው ኤልዛባድ፥ 13ዐሥረኛው ኤርምያስ፥ ዐሥራ አንደኛው መክበናይ። 14እነዚህ የጋድ ልጆች የጭፍራ አለቆች ነበሩ፤ ከእነርሱም ታናሹ የመቶ አለቃ ታላቁ የሺህ አለቃ ነበር። 15በመጀመሪያው ወር ዮርዳኖስ ከዳር እስከ ዳር ሞልቶ በነበረ ጊዜ የተሻገሩት እነዚህ ናቸው፤ በሸለቆውም ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ በኩል የተቀመጡትን ሁሉ አባረሩ።
ከብንያም ወገን ዳዊትን የተከተሉ
16ዳዊትም ወደ ነበረባት ወደ አንባዪቱ ከብንያምና ከይሁዳ ወገን ሰዎች ዳዊትን ለመርዳት መጡ። 17ዳዊትም ሊገናኛቸው ወጥቶ፥ “በሰላም ወደ እኔ መጥታችሁ እንደ ሆነ ልቤ ከእናንተ ጋር አንድ ይሆናል፤ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ መጥታችሁ እንደ ሆነ ግን፥ በእጄ ዓመፅ የለብኝምና የአባቶቻችን አምላክ ይመልከተው፥ ይፍረደውም፤” አላቸው። 18መንፈስም በሠላሳው አለቃ በዓማሣይ ላይ መጣ፤ እርሱም፥ “ዳዊት ሆይ፥ እኛ ያንተ ነን፤ የእሴይ ልጅ ሆይ፥ እኛ ከአንተ ጋር ነን፤ ውጣ አምላክህ ይረዳሃልና ሰላም ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ለሚረዱህም ሰላም ይሁን” አለ። ዳዊትም ተቀበላቸው፤ የጭፍራም አለቆች አደረጋቸው።
ከምናሴ ወገን ዳዊትን የተከተሉ
19ዳዊትም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሳኦልን ሊወጋ በመጣ ጊዜ ከምናሴ ወገን ሰዎች ወደ ዳዊት ከዱ፤ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን፥ “በራሳችን ላይ ጉዳት አድርጎ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ይመለሳል” ሲሉ ተማክረው ሰድደውታልና እርሱ አልረዳቸውም። 20ዳዊትም ወደ ሴቄላቅ ሲሄድ ከምናሴ ወገን የምናሴ ሻለቆች የነበሩ ዓድና፥ ዮዛባት፥ ይዲኤል፥ ሚካኤል፥ ዮዛባት፥ ኤሊሁና ጼልታይ ወደ እርሱ ከዱ። 21ሁሉም ጽኑዓን ኀያላንና በሠራዊቱ ላይ አለቆች ነበሩና በአደጋ ጣዮች ላይ ዳዊትን አገዙት። 22እንደ እግዚአብሔርም ሠራዊት ታላቅ ሠራዊት እስኪሆን ድረስ ዳዊትን ለመርዳት ዕለት ዕለት ይመጡ ነበር።
የዳዊት ሠራዊት ብዛት
23እንደ እግዚአብሔርም ቃል የሳኦልን መንግሥት ወደ እርሱ ይመልሱ ዘንድ በኬብሮን ሳለ ወደ ዳዊት የመጡት የሠራዊቱ አለቆች ቍጥር ይህ ነው። 24ጋሻና ጦር ተሸክመው ለሰልፍ የተዘጋጁ የይሁዳ ልጆች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ። 25ለሰልፍ ጽኑዓን ኀያላን ሰዎች የነበሩ የስምዖን ልጆች ሰባት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። 26የሌዊ ልጆች አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 27የአሮንም ቤት አለቃ ዮዳሄ ነበረ፤ ከእርሱም ጋር ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ፤ 28ከእርሱም ጋር ጽኑዕ ኀያል ጐልማሳ ሳዶቅ ነበረ፤ ከአባቱም ቤት ሃያ ሁለት አለቆች ነበሩ። 29የሳኦልም ወንድሞች ከሆኑ ከብንያም ልጆች ሦስት ሺህ ነበሩ። የሚበልጠው ክፍል የሳኦልን ቤት ይጠብቁ ነበሩ። 30ጽኑዓን ኀያላን የሆኑ በአባቶቻቸውም ቤት የታወቁ የኤፍሬም ልጆች ሃያ ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ። 31በየስማቸው የተጻፉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ የመጡ የምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ስምንት ሺህ ነበሩ። 32እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ከእነርሱ ጋር ነበሩ። 33በጭፍራውም ውስጥ ዳዊትን ለመርዳት የወጡ የተዘጋጁ፥ መሣሪያም ሁሉ የያዙ የዛብሎን ሰዎች አምሳ ሺህ ነበሩ፤ ከእነርሱ አንድስ እንኳ ደካማ አልነበረም። 34የንፍታሌምም አለቆች አንድ ሺህ ነበሩ፥ ከእነርሱም ጋር ጋሻና ጦር የሚይዙ ሠላሳ ሰባት ሺህ ነበሩ። 35ለሰልፍም የተዘጋጁ የዳን ሰዎች ሃያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ#አንዳንድ የግሪክኛ ዘርዕ “ስምንት መቶ” ይላል “ሰባት መቶ” የሚልም አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ ይገኛል። ነበሩ። 36በጭፍራውም ውስጥ የሚወጡ፥ ለሰልፍም የተዘጋጁ የአሴር ሰዎች አርባ ሺህ ነበሩ። 37በዮርዳኖስም ማዶ ካሉ ከሮቤልና ከጋድ ሰዎች ከምናሴም ነገድ እኩሌታ የጦር መሣሪያንም ሁሉ ይዘው የመጡ መቶ ሃያ ሺህ ነበሩ።
38እነዚህ ሁሉ ዳዊትን በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሡት ዘንድ አርበኞችና ሰልፈኞች እየሆኑ በፍጹም ልባቸው ወደ ኬብሮን መጡ፤ ደግሞም ከእስራኤል የቀሩት ሁሉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ አንድ ልብ ነበሩ። 39ወንድሞቻቸውም አዘጋጅተውላቸው ነበርና እየበሉና እየጠጡ በዚያ ከዳዊት ጋር#“ከዳዊት ጋር” የሚለው በግእዝ እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ሦስት ቀን ተቀመጡ። 40ደግሞም በእስራኤል ዘንድ ደስታ ሆኖአልና እስከ ይሳኮርና እስከ ዛብሎን እስከ ንፍታሌምም ድረስ ለእርሱ አቅራቢያ የነበሩ በአህያና በግመል በበቅሎና በበሬ ላይ እንጀራና ዱቄት የበለስ ጥፍጥፍና የዘቢብ ዘለላ የወይንም ጠጅ፥ ዘይትም በሬዎችንና በጎችንም፥ ፍየሎችንም#“ፍየሎችንም” የሚለው በግእዝ ብቻ። በብዙ አድርገው ያመጡ ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 12: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ