የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ሩት 1:1-18

መጽሐፈ ሩት 1:1-18 መቅካእኤ

መሳፍንት ይፈርዱ በነበረበት ዘመን በአገሩ ላይ ረሀብ ሆነ። አንድ ሰውም ከሚስቱና ከሁለቱ ልጆቹ ጋር በሞዓብ ምድር ለመቀመጥ ከቤተልሔም ይሁዳ ተነሥቶ ሄደ። የሰውዬው ስም ኤሊሜሌክ፥ የሚስቱም ስም ናዖሚ፥ የሁለቱም ልጆች ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበረ፥ እነርሱም የቤተልሔም ይሁዳም የኤፍራታ ሰዎች ነበሩ። ወደ ሞዓብም ምድር መጡ፥ በዚያም ተቀመጡ። የናዖሚም ባል ኤሊሜሌክ ሞተ፥ እርሷም ከሁለቱ ልጆችዋ ጋር ቀረች። እነርሱም ከሞዓባውያን ሴቶች ሚስት አገቡ፥ የአንዲቱ ስም ዖርፋ የሁለተኛይቱም ስም ሩት ነበረ። በዚያም ዐሥር ዓመት ያህል ተቀመጡ። መሐሎንና ኬሌዎን ሁለቱም ሞቱ፥ ሴቲቱም ሁለቱን ልጆችዋንና ባልዋን አጥታ ብቻዋን ቀረች። እርሷም በሞዓብ ምድር ሳለች ጌታም ሕዝቡን እንደ ጐበኘ እህልም እንደሰጣቸው ስለ ሰማች፥ ከሞዓብ ምድር ልትመለስ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ተነሣች። እርሷም ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ከተቀመጠችበት ስፍራ ወጣች፥ ወደ ይሁዳም ምድር ሊመለሱ መንገድ ጀመሩ። ናዖሚም ምራቶችዋን፦ “ሂዱ፥ ወደ እናቶቻችሁም ቤት ተመለሱ፥ ለእኔና ለሞቱት እንዳደረጋችሁት፥ ጌታም ቸርነት ያድርግላችሁ። ጌታም በየባላችሁ ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ” አለቻቸው። ሳመቻቸውም፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ። እነርሱም፦ “ከአንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን” አሉአት። ናዖሚም አለች፦ “ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፥ ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ለእናንተ ባሎች የሚሆኑ ልጆች በማህፀኔ ይዣለሁን? ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፥ ባል ለማግባት አርጅቻለሁና ሂዱ፥ ተስፋ አለኝ ብል፥ ዛሬ ሌሊትስ እንኳ ባል ባገባ፥ ወንዶች ልጆችም ብወልድ፥ እነርሱ እስኪያድጉ እስኪደርሱ መጠበቅ ትችላላችሁን? በእነርሱስ ምክንያት ባል ሳታገቡ ትቆያላችሁን? ልጆቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሆንም፥ እኔን ጌታ ተቈጥቶኛል፤ በእናንተም ላይ በደረሰው ነገር በጣም አዝኜአለሁ።” ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንደገና አለቀሱ፥ ዖርፋም አማቷን ሳመች፥ ሩት ግን አማቷ ጋር ተጣበቀች። እሷም፦ “እነሆ ዋርሳሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፥ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ” አለቻት። ሩት ግን እንዲህ አለች፦ “እንድተውሽ ተለይቼሽም እንድመለስ አታስገድጅኝ፤ በምትሄጅበት እሄዳለሁ፥ በምታድሪበትም አድራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ በምትቀበሪበትም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር ከአንቺ የሚለየኝ ነገር ቢኖር ጌታ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ!” ከእርሷ ጋር ለመሄድ እንደ ቈረጠች ባየች ጊዜ ናዖሚ ከመናገር ዝም አለች።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}