የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ሩት 1:1-18

መጽሐፈ ሩት 1:1-18 አማ05

በእስራኤል አገር መሳፍንት ይገዙ በነበረበት ዘመን በሀገሩ ላይ ረሀብ ሆነ፤ ከዚህም የተነሣ በይሁዳ ክፍለ ሀገር ከቤተልሔም አንድ ሰው ከሚስቱና ከሁለት ወንዶች ልጆቹ ጋር ለመኖር ወደ ሞአብ አገር ሄደ። የሰውዬው ስም ኤቤሜሌክ፥ የሚስቱ ስም ናዖሚ፥ የሁለቱ ልጆች ስም ማሕሎንና ኬሌዎን ይባል ነበር፤ በትውልዱ ኤፍራታዊ ሆኖ በቤተልሔም ከተማ የሚኖር ነበር፤ እርሱም ከቤተሰቡ ጋር ወደ ሞአብ አገር ሄዶ ኖረ። የናዖሚ ባል ኤቤሜሌክ ሞተ፤ ናዖሚም ከሁለቱ ልጆችዋ ጋር ብቻዋን ቀረች፤ ልጆችዋም ዖርፋና ሩት የተባሉትን የሞአብ አገር ልጃገረዶች አግብተው ዐሥር ዓመት ያኽል ኖሩ። ማሕሎንና ኬሌዎንም ሞቱ፤ ናዖሚም ባልዋንና ልጆችዋን አጥታ ብቻዋን ቀረች። ናዖሚ በሞአብ አገር ሳለች፥ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ምሕረት እንዳደረገላቸውና ብዙ መከር እንደ ሰጣቸው ሰማች፤ ስለዚህ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ከሞአብ ወደ እስራኤል ለመመለስ ተነሣች። ወደ ይሁዳ አገር ለመሄድም አብረው መጓዝ ጀመሩ፤ ነገር ግን በመንገድ ላይ ሳሉ፥ ናዖሚ ምራቶችዋን እንዲህ አለቻቸው፤ “እንግዲህ ወደየቤታችሁ ተመለሱና ከእናቶቻችሁ ጋር ኑሩ፤ ለእኔና ለሟቾቹ ባሎቻችሁ መልካም ነገር እንዳደረጋችሁ፥ እንዲሁም እግዚአብሔር ለእናንተ መልካም ነገር ያድርግላችሁ፤ እያንዳንዳችሁ እንደገና ባል አግብታችሁ ትዳር እንድትመሠርቱ እግዚአብሔር ይርዳችሁ።” ከዚህ በኋላ ናዖሚ ለመሰናበት ሳመቻቸው፤ እነርሱ ግን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። “አይሆንም! እኛ ከአንቺ ጋር ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን” አሉአት። ናዖሚም እንዲህ አለቻቸው፤ “ልጆቼ ሆይ! እባካችሁ ተመለሱ፤ ከእኔ ጋር ለመሄድ የምትፈልጉት ለምንድነው? ለእናንተ ባሎች የሚሆኑ ልጆች እንደገና መውለድ የምችል ይመስላችኋልን? ልጆቼ ሆይ! ወደየቤታችሁ ተመለሱ፤ እኔ ሌላ ባል እንዳላገባ ዕድሜዬ አይፈቅድልኝም፤ ለመሆኑ ለማግባት ተስፋ ቢኖረኝና ዛሬውኑ አግብቼ ልጆች ብወልድስ፥ እነርሱ ለአካለ መጠን እስኪደርሱ መጠበቅ ትችላላችሁን? በዚህስ ምክንያት ሌሎች ባሎች ሳታገቡ ትቀራላችሁን? ልጆቼ ሆይ! ይህ የማይሆን ነው፤ እኔን እግዚአብሔር ተቈጥቶኛል፤ በእናንተም ላይ በደረሰው ነገር በጣም አዝኜአለሁ” አለቻቸው። እነርሱም እንደገና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ በዚህ ጊዜ ዖርፋ ዐማትዋን ስማ ተሰናበተች፤ ሩት ግን ከዐማትዋ ላለመለየት ወሰነች። ስለዚህ ናዖሚ “ሩት ሆይ! የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖችዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፤ አንቺም ከእርስዋ ጋር ተመለሺ” አለቻት። ሩት ግን እንዲህ አለቻት፦ “ተለይቼሽ እንድመለስ አታስገድጅኝ! አንቺ ወደምትሄጂበት ሁሉ እሄዳለሁ፤ አንቺ በምትኖሪበት እኖራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ በምትቀበሪበትም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር ከአንቺ የሚለየኝ ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ይፍረድብኝ!” ሩት ከእርስዋ ጋር ለመሄድ ቊርጥ ሐሳብ ማድረጓን በተረዳች ጊዜ፥ ናዖሚ ሌላ ነገር አልተናገረችም።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}