የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ሮሜ ሰዎች 8

8
ሕይወት በመንፈስ
1ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም። 2በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቶኛልና። 3ሕግ ከሥጋ ድካም የተነሣ ማድረግ ያልቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌና ስለ ኃጢአት ልኮ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ፤ 4እንደ ሥጋ ሳይሆን እንደ መንፈስ በምንመላለስ በእኛ፥ ሕጉ የሚጠይቀው ጽድቅ እንዲፈጸም ነው። 5እንደ ሥጋ የሚኖሩ አእምሮአቸው የሥጋን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉና፥ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን አእምሮአቸው የመንፈስን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉ። 6ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። 7ስለ ሥጋ ማሰብ የእግዚአብሔር ጠላት መሆን ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም አይችልም፥ 8በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም።
9እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። ነገር ግን ማንም የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው፥ እርሱ የክርስቶስ አይደለም። 10ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፤ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። 11#1ቆሮ. 3፥16።ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፥ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ፥ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ አማካይነት፥ ለሟች አካላቶቻችሁ ሕይወትን ይሰጠዋል።
12ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! ባለዕዳ ነን፤ እንደ ሥጋ እንድንኖር ለሥጋ አይደለም፥ 13እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና የሰውነትን ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን በሕይወት ትኖራላችሁ። 14በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ፥ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። 15#ገላ. 4፥5-7።#ማር. 14፥36፤ ገላ. 4፥6።እንደገና የፍርሃት ባርያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፥ ነገር ግን “አባ! አባት!” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋል። 16የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መንፈሱ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክርልናል። 17ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ከእርሱ ጋር የክብሩ ተካፋዮች እንድንሆን ከእርሱ ጋር መከራ ብንቀበል የእግዚአብሔር ወራሾችና ከክርስቶስም ጋር አብረን ወራሾች ነን።
የሚመጣው ክብር
18 # ጥበ. 3፥5፤6። የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ወደ ፊት ለእኛ ከሚገለጥልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም ዋጋ እንደሌለው እቆጥረዋለሁ። 19ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃልና። 20#ዘፍ. 3፥17-19።ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ ይኸውም በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእርሱ ፈቃድ ነው። 21ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው የከበረውን ነፃነት እንዲያገኝ ነው። 22እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ አብሮ በመቃተትና በምጥ ሥቃይ እንደሚኖር እናውቃለንና። 23#2ቆሮ. 5፥2-4።ፍጥረት ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን እኛ ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት በናፍቆት እየተጠባበቅን እኛ ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። 24በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋው የሚታይ ከሆነ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? 25ነገር ግን ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፥ በትዕግሥት እንጠባበቃለን።
26እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ይረዳናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ያማልድልናል፤ 27ልቦችንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስ ሐሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፥ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ያማልዳልና።
28እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ ዓላማውም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። 29አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአልና፥ ይህም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኩር እንዲሆን ነው፤ 30አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህንም ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውን እነዚህንም ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን እነዚህንም ደግሞ አከበራቸው።
የእግዚአብሔር ፍቅር
31እንግዲህ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? 32ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው እርሱ፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? 33እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው። 34የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ስለ እኛም በእርግጥ የሚያማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። 35ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? መከራ ወይስ ሥቃይ፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ረሃብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ አደጋ፥ ወይስ ሰይፍ?
36 # መዝ. 44፥22። ይህም “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፤
እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን፤”
ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። 37በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። 38ይህንን ተረድቼአለሁ፤ ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ገዢዎችም ቢሆኑ፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ 39ከፍታም ቢሆን፥ ጥልቀትም ቢሆን፥ ሌላ ፍጥረትም ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}