ወደ ሮሜ ሰዎች 15:14-33

ወደ ሮሜ ሰዎች 15:14-33 መቅካእኤ

ወንድሞቼ ሆይ! እኔም ራሴ ስለ እናንተ በበጎነት ራሳችሁ እንደ ተሞላችሁ፥ እውቀትም ሁሉ እንደ ሞላባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግሞ ልትወቃቀሱ እንደምትችሉ ተረድቼአለሁ። ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችን ላስታውሳችሁ ፈልጌ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ መሰረት በድፍረት ጻፍሁላችሁ። በእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እንድሆን ነው፥ ይህም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው። እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሆነ ነገር የምመካበት አለኝ። አሕዛብ እንዲታዘዙ ክርስቶስ በቃልና በሥራ፥ በእኔ አድርጎ ከሠራው በቀር ምንም ልናገር አልደፍርም፤ በምልክትና በድንቅ ሥራ ኃይል፥ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል፥ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ። እንዲሁም በሌላው ሰው መሠረት ላይ አልሠራሁም፤ የክርስቶስ ስም ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን ለመስበክ ተጋሁ፤ ነገር ግን “ስለ እርሱ ያልተወራላቸው ያያሉ፤ ያልሰሙም ያስተውላሉ፤” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። ስለዚህ ደግሞ ወደ እናንተ እንዳልመጣ ብዙ ጊዜ ተከለከልሁ። አሁን ግን በዚህ አገር ስፍራ ከእንግዲህ ወዲያ የለኝም፥ ከብዙ ዓመታት ጀምሮም ወደ እናንተ ልመጣ ናፍቆት ስላለኝ፥ ወደ ስፔን በምሄድበት ጊዜ፥ ከእናንተ ጋር ተደስቼ ጥቂት ካሳላፍሁ በኋላ በጉዞዬ እንድትረዱኝ ሳልፍ ላያችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። አሁን ግን ቅዱሳንን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ። መቄዶንያና አካይያ በኢየሩሳሌም ካሉት ቅዱሳን መካከል ያሉትን ድሆች ለመርዳት ወደዋል። ተደስተዋልና የእነርሱ ባለ ዕዳዎች ናቸው፤ በእነርሱ መንፈሳዊ ነገር አሕዛብ ተካፋዮች ከሆኑ በሥጋዊ ነገር ደግሞ ሊያገለግሉአቸው ይገባቸዋል። ስለዚህ ይህን ፈጽሜ፥ ይህን ፍሬ ካተምሁላቸው በኋላ በእናንተ በኩል አድርጌ ወደ ስፔን እሄዳለሁ፤ ወደ እናንተም ስመጣ በክርስቶስ በረከት ሙላት እንደምመጣ አውቃለሁ። ወንድሞች ሆይ! ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ከእኔ ጋር እንድትጋደሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ፤ ይህም በይሁዳ ካሉት፥ ከማይታዘዙት እንድድን፥ ለኢየሩሳሌምም ያለኝ አገልግሎቴ በቅዱሳን ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ በደስታ ወደ እናንተ መጥቼ ከእናንተ ጋር እንዳርፍ ነው። የሰላም አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።