የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 18:17-24

የዮሐንስ ራእይ 18:17-24 መቅካእኤ

ይህን የሚያህል ታላቅ ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና፤” የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፤ የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ “ታላቂቱን ከተማ የምትመስል ሌላ ከተማ ነበረችን?” እያሉ ጮኹ። በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ “በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከሀብቷ የተነሣ ሀብታም ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና፤” እያሉ ጮኹ። “ሰማይ ሆይ! ቅዱሳን፥ ሐዋርያትና ነቢያት ሆይ! ስለተፈረደባት በእርሷ ላይ ደስ ይበላችሁ፤ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና።” አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንሥቶ እንዲህ ሲል ወደ ባሕር ወረወረው “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም። ከእንግዲህ ወዲህ በገና የሚመቱና የሚዘምሩ ሰዎች ድምፅ፥ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ሰዎች ድምፅ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ የማንኛውም ዕደ ጥበብ ብልሃተኛ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፤ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፤ የሙሽራውና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፤ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና።” በእርሷም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም፥ በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።