ለሰባቱም መላእክት “ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ፤” የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱ ሰማሁ። የመጀመሪያውም መልአክ ሄዶ ጽዋውን በምድር ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ላይ ክፉኛ የሚነዘንዝ ቁስል ሆነባቸው። ሁለተኛውም መልአክ ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ ባሕሩም የሞተ ሰው ደም መሰለ፤ በባሕርም ውስጥ ሕይወት ያለው ነፍስ ሁሉ ሞተ። ሦስተኛውም መልአክ ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ። የውሃውም መልአክ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ! ቅዱስ ሆይ! እንዲህ ስለ ፈረድህ ጻድቅ ነህ፤ የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፤ የሚገባቸው ነውና፤” ከመሠዊያውም “አዎን፤ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው፤” ብሎ ሲናገር ሰማሁ። አራተኛውም መልአክ ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት እንድታቃጥል ሥልጣን ተሰጣት። ሰዎችም በታላቅ ትኩሳት ተቃጠሉ፤ በነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፤ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሓ አልገቡም። አምስተኛውም መልአክ ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች፤ ከስቃይም የተነሣ ሰዎች መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፤ ከስቃያቸውና ከቁስላቸውም የተነሣ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፤ ከሥራቸውም ንስሓ አልገቡም። ስድስተኛውም መልአክ ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውሃው ደረቀ። ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ፥ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጉንቸሮችን የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥ ምልክት እያደረጉ፥ በታላቁና ሁሉን በሚገዛው በእግዚአብሔር ቀን ለሚሆነው ጦርነት እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ። “እነሆ እንደ ሌባ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ ኀፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ እስከተቱአቸው። ሰባተኛውም መልአክ ጽዋውን በአየር ላይ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ “ተፈጸመ!” የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ።
የዮሐንስ ራእይ 16 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ራእይ 16
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ራእይ 16:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች