የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙረ ዳዊት 45

45
1ለመዘምራን አለቃ፥ በመለከቶች፥ የቆሬ ልጆች ትምህርት፥ የፍቅር መዝሙር።
2ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ፥
እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ፥
አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሓፊ ብርዕ ነው።
3 # መኃ. መኃ. 5፥10-16። ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል፥
ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ፥
ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ባረከህ።
4 # መዝ. 21፥5። ኃያል ሆይ፥ በግርማህና በውበትህ
ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ።
5ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም
አቅና ተከናወን ንገሥም፥
ቀኝህም በክብር ይመራሃል።
6ኃያል ሆይ፥ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፥
እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ፥
አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ።
7 # ዕብ. 1፥8-9። አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው፥
የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው።
8ጽድቅን ወደድህ ዓመፃንም ጠላህ፥
ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ
እግዚአብሔር አምላክ የደስታ ዘይትን ቀባህ።
9በልብሶችህ ሁሉ ከርቤና ሽቱ ዝባድም አሉ፥
በዝሆን ጥርስ ከተዋቡ ቤተ መንግሥቶች ይልቅ
የበገናና የመሰንቆ ድምጽ ደስ ያሰኙሃል።
10የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፥
በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ
ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።
11ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፥
ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፥
12ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥
እርሱ ጌታሽ ነውና እጅ ንሺው።
13 # መዝ. 72፥10-11፤ ኢሳ. 60፥5። የጢሮስ ሴት ልጅ፥
የምድር ባለ ጠጎች አሕዛብ በፊትሽ ደጅ ይጠናሉ።
14 # ሕዝ. 16፥10-13። ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው፥
ልብስዋ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው።
15በኋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ፥
ባልንጀሮችዋንም ወደ አንተ ያቀርባሉ፥
16በደስታና በሐሴት ይወስዱአቸዋል፥
ወደ ንጉሥ እልፍኝም ያስገቡአቸዋል።
17 # ዘፍ. 17፥6። በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ፥
በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ።
18 # ኢሳ. 60፥15። ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ፥
ስለዚህ ለዓለምና ለዘለዓለም አሕዛብ ይገዙልሃል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ