የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙረ ዳዊት 18:25-50

መዝሙረ ዳዊት 18:25-50 መቅካእኤ

ጌታም እንደጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዐይኖቹ ፊት መለሰልኝ። ከታማኝ ሰው ጋር ታማኝ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፥ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከጠማማም ጋር ብልህ ሆነህ ትገኛለህ። አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዐይን ግን ታዋርዳለህ። አንተ መብራቴን ታበራለህና፥ ጊታ አምላኬ ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ግብረ ኃይል አጠቃለሁ፥ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁ። የአምላኬ መንገድ ፍጹም ነው፥ የጌታም ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው። ከጌታ በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችን በቀር አምላክ ማን ነው? ኃይልን የሚያስታጥቀኝ መንገዴንም የሚያቃና፥ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያበረታ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው። እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፥ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ። ለደኅንነቴም ጋሻን ሰጠኸኝ፥ ቀኝህም ትረዳኛለች፥ ትምህርትህም አሳደገችኝ፥ አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም። ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ እይዛቸዋለሁም፥ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም። አስጨንቃቸዋለሁ፥ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ። ለጦርነት ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፥ በበላዬ የቆሙትን ሁሉ በበታቼ ታስገዛቸዋለህ። የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋቸዋለሁ። ጮኹ የሚረዳቸውም አልነበረም፥ ወደ ጌታ ጮኹ፥ ነገር ግን አልመለሰላችውም። እንደ ትቢያ በነፋስ ፊት እፈጫቸዋለሁ፥ እንደ አደባባይም ጭቃ እረግጣቸዋለሁ። ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፥ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፥ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል። በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ፥ የባዕድ ልጆች ያጐነብሱልኛል። የባዕድ ልጆች ጠወለጉ፥ በመንቀጥቀጥም ከምሽጋቸው ወጥተው ወደ እኔ መጡ። ጌታ ሕያው ነው፥ አምላኬም መጠጊያዬ ቡሩክ ነው፥ የመድኃኒቴም አምላክ ከፍ ከፍ ይበል። በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ አሕዛብን በበታቼ ያስገዛልኛል። ከጠላቶቼ የሚታደገኝ እርሱ ነው፥ በእኔም ላይ ከቆሙት በላይ ታደርገኛለህ፥ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ። አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ።