የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 18:25-50

መጽሐፈ መዝሙር 18:25-50 አማ05

አምላክ ሆይ! ለአንተ ታማኞች ለሆኑት ታማኝ ነህ፤ እውነተኞች ለሆኑትም እውነተኛ ነህ። ለንጹሖች ንጹሕ ነህ፤ ለጠማሞች ግን ተገቢ ዋጋቸውን ትሰጣለህ። ትሑቶችን ታድናለህ፤ ትዕቢተኞችን ግን ታዋርዳለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ለእኔ ብርሃኔ ነህ፤ አንተ አምላኬ ጨለማዬን ታበራለህ። በአንተ ርዳታ አንድ የጦር ጓድ አጠቃለሁ፤ አንተ አምላኬም ቅጥሩን ለመዝለል ትረዳኛለህ። የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው! ቃሉም ተጠራ ነው! እርሱን መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው። ከእግዚአብሔር በቀር ማነው አምላክ? ከእርሱስ በቀር መጠጊያ የሚሆን ማነው? ብርታትን የሚሰጠኝና መንገዴን የሚያቀናልኝ እግዚአብሔር ነው። እርሱ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያጠነክራል፤ በከፍታ ቦታዎችም ያለ ስጋት ለመቆም ያስችለኛል። እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤ የነሐስን ቀስት መሳብ እንዲችሉ ክንዶቼን ያበረታል። የማዳን ጋሻህን ሰጠኸኝ፤ ቀኝ እጅህም ይጠብቀኛል፤ እኔን ለመርዳት መጥተህ ታላቅ አደረግኸኝ። መረማመጃዬን አሰፋህ፤ እግሮቼም አልተንሸራተቱም። ጠላቶቼን አሳድጄ እደርስባቸዋለሁ፤ ሳላጠፋቸውም ወደ ኋላ አልመለስም። ዳግመኛ እንዳይነሡ አድርጌ እመታቸዋለሁ፤ በእግሬም ሥር ይወድቃሉ። ለጦርነት ኀይልን ትሰጠኛለህ፤ በጠላቶቼም ላይ ድልን ታጐናጽፈኛለህ። ጠላቶቼ ከፊቴ ወደ ኋላ እንዲሸሹ አደረግህ የሚጠሉኝንም ሁሉ አጠፋቸዋለሁ። የሚረዳቸውን በመፈለግ ይጮኻሉ፤ ነገር ግን ማንም አያድናቸውም፤ እግዚአብሔርንም ይጠሩታል፤ እርሱ ግን አይመልስላቸውም። ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ እስኪሆኑ ድረስ አደቃቸዋለሁ፤ በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃም እረግጣቸዋለሁ። ከዐመፀኛ ሕዝብ አዳንከኝ፤ በአሕዛብም ላይ ሾምከኝ፤ የማላውቀውም ሕዝብ ይገዛልኛል። ባዕዳን ያጐነብሱልኛል፤ ዝናዬን እንደ ሰሙም ይገዙልኛል። በፍርሃት ይጨነቃሉ፤ በመንቀጥቀጥም ከምሽጋቸው ወጥተው ወደ እኔ ይመጣሉ። እግዚአብሔር ሕያው ነው! አምላኬ መጠጊያዬ ይመስገን! ያዳነኝም ኀያል አምላክ ከፍ ከፍ ይበል። እርሱ ጠላቶቼን ይበቀልልኛል፤ ሕዝቦችንም ከበታቼ አድርጎ ያስገዛልኛል። ከጠላቶቼም ታድነኛለህ። ከጠላቶቼ በላይ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤ ከግፈኞችም ታድነኛለህ። እግዚአብሔር ሆይ! ስለዚህ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ። እርሱ ላነገሠው ንጉሥ ታላቅ ድልን ያጐናጽፈዋል፤ ራሱ ለቀባው ዘለዓለማዊ ፍቅሩን ያሳየዋል፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘለዓለም ይህን ያደርጋል።