የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙረ ዳዊት 119:113-128

መዝሙረ ዳዊት 119:113-128 መቅካእኤ

ዓመፀኞችን ጠላሁ፥ ሕግን ግን ወደድሁ። አንተ ረዳቴና መጠጊያዬ ነህ፥ በቃልህም ተማመንሁ። እናንተ ኃጢአተኞች፥ ከእኔ ራቁ፥ የአምላኬንም ትእዛዝ ልፈልግ። እንደ ቃልህ ደግፈኝ፥ ሕያውም እሆናለሁ፥ ከተስፋዬም አልፈር። እርዳኝ እድናለሁም፥ ሁልጊዜም ሥርዓትህን እመረምራለሁ። ምኞታቸው ዓመፃ ነውና ከሥርዓትህ የሚርቁትን ሁሉ አጐሳቈልሃቸው። የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ እንደ ርኩሰት አጠፋሃቸው፥ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። ሥጋዬ አንተን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ፥ ከፍርድህ የተነሣ ፈርቻለሁ። ፍርድንና ጽድቅን ሠራሁ፥ ለሚያስጨንቁኝ አሳልፈህ አትስጠኝ። ባርያህን በመልካም ጠብቀው፥ ትዕቢተኞችም አይጋፉኝ። ዐይኖቼ ለማዳንህ፥ ለጽድቅህም ቃል ፈዘዙ። ለባርያህ እንደ ምሕረትህ አድርግ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ። እኔ ባርያህ ነኝ፥ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ምስክርህንም አውቃለሁ። ለጌታ የሥራ ጊዜ ነው፥ ሕግህንም ሻሩት። ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቁ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ። ስለዚህ ወደ ትእዛዝህ ሁሉ አቀናሁ፥ የዓመፅንም መንገድ ሁሉ ጠላሁ።