መዝሙረ ዳዊት 118:1-14

መዝሙረ ዳዊት 118:1-14 መቅካእኤ

ሃሌ ሉያ! ጌታን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና። ቸር እንደሆነ፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም እንደሆነ የእስራኤል ቤት አሁን ይንገሩ። ቸር እንደሆነ፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም እንደሆነ የአሮን ቤት አሁን ይንገሩ። ቸር እንደሆነ፥ ፍቅሩም ለዘለዓለም እንደሆነ ጌታን የሚፈሩ ሁሉ አሁን ይንገሩ። በተጨነቅሁ ጊዜ ጌታን ጠራሁት፥ መለሰልኝ፥ አሰፋልኝም። ጌታ ከጎኔ ነው፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል? ጌታ ሊረዳኝ ከጎኔ ነው፥ እኔም ጠላቶቼን በኩራት አያለሁ። በሰው ከመታመን ይልቅ በጌታ መጠለል ይሻላል። በኃያላን ከመታመን ይልቅ በጌታ መጠለል ይሻላል። አሕዛብ ሁሉ ከበቡኝ፥ በጌታ ስም አጠፋኋቸው፥ መክበቡንስ ከበቡኝ፥ በጌታ ስም አጠፋኋቸው። ንብ ማርን እንዲከብብ ከበቡኝ፥ እሳትም በእሾህ ውስጥ እንደሚነድድ ነደዱ፥ በጌታ ስም አጠፋኋቸው። ገፈተሩኝ፥ ለመውደቅም ተንገዳገድሁ፥ ጌታ ግን አገዘኝ። ኃይሌም ዝማሬዬም ጌታ ነው፥ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ።