የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 118:1-14

መጽሐፈ መዝሙር 118:1-14 አማ05

ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ እግዚአብሔርን አመስግኑ። የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ “የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ። የእግዚአብሔር ካህናት የሆኑት የአሮን ልጆች ሁሉ “የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ። የሚፈሩት ሁሉ “የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ። በተጨነቅሁ ጊዜ ጩኸቴን ወደ እግዚአብሔር አሰማሁ፤ እርሱም ሰማኝ፤ ነጻም አወጣኝ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚረዳኝ አልፈራም፤ ከቶ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል? እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚረዳኝ፥ የጠላቶቼን ውድቀት አያለሁ። በሰው ከመመካት ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። በመሪዎች ከመመካት ይልቅ፥ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። ብዙ ሕዝቦች ከበውኝ ነበር፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኀይል ደመሰስኳቸው። ከየአቅጣጫው በዙሪያዬ ነበሩ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኀይል ደመሰስኳቸው። ዙሪያዬን እንደ ንብ ከበቡኝ፤ ነገር ግን እሾኽ በእሳት እንደሚቃጠል በፍጥነት ተቃጠሉ፤ በእግዚአብሔርም ኀይል ደመሰስኳቸው። ብርቱ ጥቃት ደርሶብኝ፥ ለመውደቅ ተቃርቤ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ረዳኝ። እግዚአብሔር ከለላዬና መከላከያዬ ነው፤ አዳኜም እርሱ ነው።