መዝሙረ ዳዊት 106:34-48

መዝሙረ ዳዊት 106:34-48 መቅካእኤ

ጌታ እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፥ ከአሕዛብም ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ። ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ ወጥመድም ሆኑባቸው። ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ፥ የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች የሠዉአቸውን ንጹሕ ደም አፈሰሱ፥ ምድርም በደም ረከሰች። በሥራቸው ረከሱ፥ በድርጊታቸውም አመነዘሩ። የጌታም ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፥ ርስቱንም ተጸየፈ። በአሕዛብም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ የሚጠሉአቸውም ገዙአቸው። ጠላቶቻቸውም ግፍ አደረጉባቸው፥ ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ። ብዙ ጊዜ አዳናቸው፥ እነርሱ ግን በምክራቸው አስመረሩት፥ በስሕተታቸውም ተዋረዱ። እርሱ ግን ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ ጭንቃቸውን ተመለከተ፥ ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ጽኑ ፍቅሩም ብዛት ተጸጸተ። በማረኩአቸውም ሁሉ ፊት ሞገስን ሰጣቸው። ጌታ አምላካችን ሆይ፥ አድነን፥ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን። ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ፥ ሕዝብም ሁሉ አሜን ይበል። ሃሌ ሉያ።