የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 106:34-48

መጽሐፈ መዝሙር 106:34-48 አማ05

እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት አሕዛብን አላጠፉም፤ እንዲያውም ከእነርሱ ጋር ተደባልቀው የኑሮ ሥርዓታቸውን ተከተሉ። የእግዚአብሔር ሕዝቦች የአሕዛብን ጣዖቶች አመለኩ፤ ይህም ለጥፋታቸው ምክንያት ሆነ። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንትና በከነዓን አገር ለሚገኙ ጣዖቶች መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። እነርሱ ለከነዓን ጣዖቶች መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡአቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በመግደል ንጹሕ ደም አፍስሰዋል፤ ምድሪቱም በደም ረከሰች። እነርሱ በሥራቸው ረከሱ፤ በክፉ ሥራቸውም እግዚአብሔርን ካዱ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ተቈጣ፤ እጅግም ተጸየፋቸው። ለአሕዛብ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ጠላቶቻቸውም ገዥዎቻቸው ሆኑ። በጠላቶቻቸው ተጨቊነው ፈጽሞ የእነርሱ ተገዢዎች ሆኑ። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ሕዝቡን ታድጎአቸዋል፤ እነርሱ ግን በእርሱ ላይ ማመፅን መረጡ፤ ስለዚህ ኃጢአታቸው ለውድቀታቸው ምክንያት ሆነ። ይህም ሁሉ ሆኖ እንደገና ወደ እግዚአብሔር በሚጮኹበት ጊዜ ይሰማቸው ነበር፤ ሥቃያቸውንም ይመለከት ነበር። እነርሱን ለማዳን ቃል ኪዳኑን ያስታውስ ነበር፤ ስለ ታላቅ ፍቅሩም ምሕረት ያደርግላቸው ነበር። የሚጨቊኑአቸው ሁሉ እንዲራሩላቸው አደረገ። እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! አድነን! ከመንግሥታት መካከል መልሰህ ወደ አገራችን አግባን፤ በዚያን ጊዜ እናመሰግንሃለን፤ ቅዱስ ስምህንም እናከብራለን። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን! ሕዝቡ ሁሉ አሜን አሉ፤ እግዚአብሔርንም አመስግኑ።