የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙረ ዳዊት 104

104
1ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ፥
አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፥
ክብርንና ግርማን ለበስህ።
2 # ምሳ. 8፥27-28፤ ኢዮብ 9፥8፤ ኢሳ. 40፥22፤ ዘፍ. 1፥6-7፤ አሞጽ 9፥6። ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ፥
ሰማይንም እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘረጋህ፥
3እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥
ሠረገላውን ደመና የሚያደርግ፥
በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥
4 # ዕብ. 1፥7። ነፋሳትን መልእክተኞቹ የሚያደርግ፥
የእሳት ነበልባልም አገልጋዮቹ።
5ለዘለዓለም እንዳትናወጥ
ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት።
6በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንሃት፥
በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ።
7 # መዝ. 29፥3። ከቁጣህም ይሸሻሉ፥
ከነጐድጓድህም ድምፅ ይደነብራሉ፥
8ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥
ወደ ቈላዎች፥ ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ ይወርዳሉ፥
9 # ኤር. 5፥22፤ ዘፍ. 9፥11-15። እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው
ተመልሰው ምድርን እንዳይከድኑ።
10ምንጮችን ወደ ሸለቆዎች ይልካል፥
በተራሮችም መካከል ያልፋሉ፥
11 # መዝ. 147፥8-9። የዱር አራዊትን ሁሉ ያጠጣሉ፥
የበረሃ አህያዎችም ጥማቸውን ያረካሉ።
12የሰማይም ወፎች በእነርሱ ዘንድ ያድራሉ፥
በቅጠሎች መካከል#104፥12 ሰባ ሊቃናት “በድንጋዩ ስንጥቅ መካከልም” ይላል። ያዜማሉ ይጮኻሉ።
13ተራሮችን ከላይ የምታጠጣቸው፥
ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች።
14እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ
ሣርን ለእንስሳ፥
ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም ያበቅላል።
15ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥
ዘይትም ፊትን ያበራል፥
እህልም የሰውን ጉልበት ያጠነክራል።
16የጌታ ዛፎች
እርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ይጠግባሉ።
17 # ሕዝ. 31፥6። በዚያም ወፎች ጎጆአቸውን ይሠራሉ፥
ሽመላዎችም ከበላያቸው ቤታቸውን ያበጃሉ።
18ረጃጅም ተራራዎች ለዋላዎች፥
ድንጋዮችም ለእሽኮኮች መሸሻ ናቸው።
19 # ሲራ. 43፥6። ወቅቶችን ለማመልከት ጨረቃን አደረግህ፥
ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል።
20ጨለማን ታስቀምጣለህ፥ ሌሊትም ይሆናል፥
በእርሱም የዱር አራዊት ሁሉ ይወጡበታል።
21 # ኢዮብ 38፥39። የአንበሳ ግልገሎች ለመንጠቅ ይጮኻሉ፥
ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ።
22ፀሐይ ስትወጣ ይሰበሰባሉ፥
በየዋሻቸውም ይተኛሉ።
23ሰው ወደ ተግባሩ፥
እስኪመሽም ድረስ ወደ ሥራው ይወጣል።
24 # መዝ. 92፥6፤ ሲራ. 39፥16። አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፥
ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥
ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች።
25 # ሲራ. 43፥26። ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፥
በዚያ ስፍር ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥
ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ።
26 # ኢዮብ 3፥8፤ 40፥25፤29። በዚያ ላይ መርከቦች ይሄዳሉ፥
በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ያጫውትሃል#104፥26 በባሕር ውስጥ ይጫወታል፥ ይጫወትበታል የሚል ትርጉምም ሊኖረው ይችላል።
27 # መዝ. 136፥25፤ 145፥15-16። ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ
እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ።
28በምትሰጣቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፥
እጅህን ትከፍታለህ፥ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ።
29 # መዝ. 90፥3፤ ኢዮብ 34፥14-15፤ መክ. 3፥20። ፊትህን ስትሰውር ይደነግጣሉ፥
ነፍሳቸውን ታወጣለህ ይሞታሉም፥
ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ።
30መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥
የምድርንም ፊት ታድሳለህ።
31የጌታ ክብር ለዘለዓለም ይሁን፥
ጌታ በሥራው ደስ ይለዋል።
32 # መዝ. 144፥5። ምድርን ያያል እንድትንቀጠቀጥም ያደርጋል፥
ተራሮችን ይዳስሳል፥ ይጤሳሉም።
33 # መዝ. 146፥2። በሕይወቴ ሳለሁ ለጌታ እቀኛለሁ፥
ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ እዘምራለሁ።
34ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጠው፥
እኔም በጌታ ደስ ይለኛል።
35ኀጥኣን ከምድር ይጥፉ፥
ዓመፀኞች ከእንግዲህ አይገኙ።
ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ። ሃሌ ሉያ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ