መጽሐፈ ምሳሌ 4:10-19

መጽሐፈ ምሳሌ 4:10-19 መቅካእኤ

ልጄ ሆይ፥ ስማ፥ ንግግሬንም ተቀበል፥ የሕይወትህም ዓመታት ይበዙልሃል። የጥበብን መንገድ አስተማርሁህ፥ በቀናች ጎዳና መራሁህ። በሄድህ ጊዜ እርምጃህ አይታገድም፥ ብትሮጥም አትሰናከልም። ተግሣጽን ያዝ፥ አትተውም፥ ጠብቀው፥ እርሱ ሕይወትህ ነውና። በክፉዎች መንገድ አትግባ፥ በመጥፎ ሰዎችም ጎዳና አትሂድ። ከእርሷ ራቅ፥ አትሂድባትም፥ ራቅ በል ተዋትም። ክፉ ካላደረጉ አይተኙምና፥ ካላሰናከሉም እንቅልፋቸው ይወገዳልና። የክፋትን እንጀራ ይበላሉና፥ የግፍንም ወይን ጠጅ ይጠጣሉና። የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል። የክፋት መንገድ እንደ ጨለማ ነው፥ እንዴት እንደሚሰናከሉም አያውቁም።