የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 16

16
1የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው፥
የምላስ መልስ ግን ከጌታ ዘንድ ነው።
2የሰው መንገድ ሁሉ በዐይኖቹ ፊት ንጹሕ ነው፥
ጌታ ግን መንፈስን ይመዝናል።
3ሥራህን ለጌታ አደራ ስጥ፥
አሳብህም ትጸናለች።
4ጌታ ሁሉን ለእርሱ ለራሱ ፈጠረ፥
ኀጥእን ደግሞ ለክፉ ቀን።
5በልቡ የታበየ ሁሉ በጌታ ዘንድ ርኩስ ነው፥
እጅ በእጅም ሳይቀጣ አይቀርም።
6 # ጦቢ. 12፥9። በምሕረትና በእውነት ኃጢአት ትሰረያለች፥
ጌታንም በመፍራት ሰው ከክፋት ይመለሳል።
7የሰው አካሄድ ጌታን ደስ ያሰኘው እንደሆነ፥
በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል።
8 # ጦቢ. 12፥8። በጽድቅ የሚገኝ ጥቂት ነገር
በዓመፅ ከሚገኝ ከብዙ ትርፍ ይሻላል።
9የሰው ልብ መንገዱን ያዘጋጃል፥
ጌታ ግን አካሄዱን ያቀናለታል።
10የእግዚአብሔር ብይን በንጉሥ አፍ ነው፥
አፉም በፍርድ አይስትም።
11እውነተኛ ሚዛንና መመዘኛ የጌታ ናቸው፥
የከረጢት መመዘኛዎች ሁሉ የእርሱ ሥራ ናቸው።
12ግፍን መሥራት በንጉሥ ዘንድ ጸያፍ ነገር ነው፥
ዙፋን በጽድቅ ይጸናልና።
13የጽድቅ ከንፈር የነገሥታት ደስታ ናት፥
በቅን የሚናገር እርሱንም ይወድዱታል።
14የንጉሥ ቁጣ እንደ ሞት መልእክተኛ ነው፥
ጠቢብ ሰው ግን ያቈላምጠዋል።
15የንጉሥ ፊት ሲፈካ ብርሃን አለ፥
መልካም ፈቃዱም እንደ በልግ ዝናብ ደመና ነው።
16ጥበብን ማግኘት ምንኛ ከወርቅ ይሻላል!
ማስተዋልንም ማግኘት ከብር ይልቅ የሚመረጥ ነው።
17የቅኖች መንገድ ከክፋት መራቅ ነው፥
መንገዱን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃታል።
18ትዕቢት ጥፋትን፥
ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።
19ከዕቡያን ጋር ምርኮ ከመካፈል
ከትሑታን ጋር በተዋረደ መንፈስ መሆን ይሻላል።
20ቃልን የሚያዳምጥ መልካም ነገርን ያገኛል፥
በጌታ የታመነ ምስጉን ነው።
21ልቡ ጠቢብ የሆነ አስተዋይ ይባላል፥
በከንፈሩም ጣፋጭ የሆነ ትምህርትን ያበዛል።
22ገንዘብ ላደረገው ሰው እውቀት የሕይወት ምንጭ ነው፥
ስንፍና ግን የሰነፎች ቅጣት ነው።
23የጠቢብ ልብ አፉን ያስተምራል፥
ለከንፈሩም ትምህርትን ይጨምራል።
24ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፥
ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው።
25 # ምሳ. 14፥12። ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፥
ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።
26ሠራተኛን የዕለት ጉርስ ፍላጎቱ ታታሪ ያደርገዋል፥
ረሀቡ ይጐተጉተዋልና።
27ምናምንቴ ሰው ክፋትን ይምሳል፥
በከንፈሩም የሚቃጠል እሳት አለ።
28 # ሲራ. 28፥13-26። ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፥
ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል።
29ግፈኛ ሰው ወዳጁን ያባብላል፥
መልካምም ወዳይደለ መንገድ ይመራዋል።
30ዓይኑን የሚዘጋ ጠማማ አሳብን ያስባል፥
ከንፈሩን የሚነክስ ክፋትን ይፈጽማል።
31የሸበተ ጠጉር የክብር ዘውድ ነው፥
እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል።
32ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፥
ስሜቱን የሚገዛ ከተማ ከሚወስድ ይበልጣል።
33ዕጣ በጉያ ይጣላል፥
መደብዋ ሁሉ ግን ከጌታ ዘንድ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ