የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4:1-13

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4:1-13 መቅካእኤ

ስለዚህ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ደስታዬና አክሊሌ ናችሁ፤ የተወደዳችሁ ሆይ! በዚህ መንገድ በጌታ ጸንታችሁ ቁሙ። በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ፤ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ! ከእኔ ጎን በመቆም ከቀለሜንጦስ ጋር አብረው በወንጌል ሥራ ተጋድለዋልና እነዚህን ሴቶችና የተቀሩትን በሕይወት መጽሐፍ የተጻፉትን ከእኔ ጋር አብረው የሚሠሩትን እንድትረዱአቸው እለምንሃለሁ። ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፤ ደስ ይበላችሁ። ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። ጌታ መምጫው ቀርቦአል። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በምንም ዓይነት ነገር አትጨነቁ። ከሰውም ማስተዋል ሁሉ በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ክቡር የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ምስጉን የሆነውን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም ሁሉ አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደገና ማሰብ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ተሰኝቻለሁ፤ አጋጣሚዎች አልተመቻቹላችሁም እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። ይህን ስል ስለሚያስፈልገኝ ነገር እያማረርሁ አይደለም፤ ያለኝ ነገር ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ጥቂትም ማግኘትን አውቃለሁ፤ ብዙም ማግኘትን አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ የመጥገብንና የመራብን ብዙ የማግኘትንና የማጣትን ምሥጢር ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን ነገር ማድረግ እችላለሁ።