የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ፊልጵስዩስ 4:1-13

ፊልጵስዩስ 4:1-13 NASV

ስለዚህ የምወድዳችሁና የምናፍቃችሁ፣ ወንድሞቼ ደስታዬና አክሊሌ የሆናችሁ፣ እንዲሁም ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ሁኔታ በጌታ ጸንታችሁ ቁሙ! በጌታ አንድ ሐሳብ እንዲኖራቸው ኤዎድያንን እለምናለሁ፤ ሲንጤኪንንም እለምናለሁ። አዎን፤ አንተ ታማኝ ባልደረባዬ ሆይ፤ ወንጌልን በማሠራጨት ረገድ ከእኔና ከቀሌምንጦስ ጋራ እንዲሁም ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከሌሎች የሥራ ጓደኞቼ ጋራ የተጋደሉትን እነዚህን ሴቶች እንድትረዳቸው እለምንሃለሁ። ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ! ገርነታችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ። ከእኔ የተማራችሁትን ወይም የተቀበላችሁትን፣ የሰማችሁትን ወይም ያያችሁትን ማንኛውንም ነገር አድርጉ፤ የሰላም አምላክም ከእናንተ ጋራ ይሆናል። ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደ አዲስ ስለ እኔ ማሰብ በመጀመራችሁ፣ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በርግጥ በተግባር ለመግለጽ ዕድሉ አልነበራችሁም እንጂ ማሰቡንስ ታስቡልኝ ነበር። ይህን የምለው ስለ ቸገረኝ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን፣ ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብ፣ ባገኝም ሆነ ባጣ፣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ። ኀይልን በሚሰጠኝ በርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ።