የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3

3
እውነተኛ ጽድቅ
1በቀረውስ ወንድሞቼ ሆይ! በጌታ ደስ ይበላችሁ። ለእናንተ ተመሳሳይ የሆነን ነገር መልሼ ለመጻፍ ለእኔ አይታክተኝም፤ ይህ ለእናንተ ለደኅንነት የሆነ ነውና።
2ከውሾች ተጠበቁ፤ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፤ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። 3እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን በእውነትም ከተገረዙት ወገን የሆንን ነንና። 4እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት ነገር ያለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። 5#ሮሜ 11፥1፤ የሐዋ. 23፥6፤ 26፥5።በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ 6#የሐዋ. 8፥3፤ 22፥4፤ 26፥9-11።ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። 7ነገር ግን ለእኔ ጥቅም የሚያስገኘውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። 8አዎን፤ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ ለማወቅ ስል ሁሉ ነገር ጉዳት እንደሆነ አድርጌ እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ነገሮች በማጣት ተጐዳሁ፤ እነርሱንም እንደ ጉድፍ አድርጌ ቈጠርኋቸው፤ በዚህም ክርስቶስን እንዳገኝ፥ 9በክርስቶስም በማመን በእምነት ላይ የተመሠረተውን የእግዚአብሔርን ጽድቅ እንጂ በሕግ ላይ የተመሠረተውን የራሴ ጽድቅ ሳይኖረኝ፥ በእርሱ እንድገኝ ነው፤ 10በሞቱም እርሱን በመምሰል ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኃይል መከራውንም ተካፋይ መሆኔን ማወቅ እፈልጋለሁ፤ 11ምናልባትም ቢሆንልኝ የሙታን ትንሣኤን እቀዳጃለሁ።
ወደ ግብ ለመድረስ መሮጥ
12እኔ ግን አሁን ይህን አላገኘሁትም ወይም አሁን ፍጹም ለመሆን አልበቃሁም፤ ዳሩ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ የራሱ አድርጎኛልና ይህን የራሴ ለማድረግ ወደ ፊት እሮጣለሁ። 13ወንድሞች ሆይ! እኔ ግን ይህንን ነገር የራሴ አድርጌዋለሁ ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ ወደ ፊት እዘረጋለሁ፤ 14በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ያለውን የመጠራት ሽልማት እንዳገኝ ወደ ግቡ እሮጣለሁ። 15እንግዲህ በአእምሮ የበሰልን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ 16ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ።
17 # 1ቆሮ. 4፥16፤ 11፥1። ወንድሞች ሆይ፤ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም ለእናንተ ምሳሌ እንደ ሆንን እንዲሁ የሚመላለሱትን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። 18ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ ነገርኋችሁ፤ አሁንም እያነባሁ ስለ እነርሱ እነግራችኋለሁ። 19መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ሐሳባቸው ምድራዊ ነው። 20እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፤ ከዚያም የሚመጣውን አዳኝ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ 21እርሱም ደግሞ ለራሱ ሁሉን ነገር በሥሩ ለማስገዛት በሚችልበት ኃይሉ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}