የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 9

9
የፋሲካ በዓል በሲና ምድረ በዳ መከበሩ
1 # ዘፀ. 12፥1-13። ከግብጽም ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሲና ምድረ በዳ ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“የእስራኤል ልጆች በተወሰነለት ጊዜ የፋሲካን በዓል ያክብሩ፤ 3በዚህ ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ምሽት ላይ፥ በተወሰነለት ጊዜ ታደርጉታላችሁ፤ እንደ ሥርዓቱ ሁሉ እንደ ደንቡም ሁሉ ታደርጉታላችሁ።” 4ሙሴም የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው። 5በመጀመሪያውም ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በሲና ምድረ በዳ የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ። 6የሞተ ሰው ሬሳን በመንካት የረከሱ ሰዎችም ነበሩ፥ ስለዚህም በዚያ ቀን የፋሲካን በዓል ለማክበር አልቻሉም ነበር። በዚያም ቀን በሙሴና በአሮን ፊት ቀረቡ። 7እነዚያም ሰዎች እርሱን እንዲህ አሉት፦ “የሞተውን ሰው ሬሳ በመነንካት ብንረክስም እንኳ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል የጌታን ቁርባን በተወሰነለት ጊዜ እንዳናቀርብ ለምን እንከለከላለን?” 8ሙሴም፦ “ጌታ ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስክሰማ ድረስ ጠብቁ” አላቸው።
9ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ከእናንተ ወይም ከትውልዶቻችሁ ዘንድ ሰው ሬሳን በመንካት ቢረክስ፥ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ፥ እርሱ እንዲህም ሆኖ እንኳ ለጌታ የፋሲካን በዓል ያክብር። 11በዓሉንም በሁለተኛው ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ምሽት ላይ ያክብሩ፤ እርሾ ካልገባበት ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። 12#ዘፀ. 12፥46፤ ዮሐ. 19፥36።ከእርሱም እስከ ማግስቱ ጥዋት ድረስ ምንም አያስቀሩ፥ ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ፤ እንደ ፋሲካ ሥርዓት ሁሉ ያክብሩት። 13ነገር ግን ንጹሕ የሆነ ሰው በመንገድም ላይ ያልሆነ የፋሲካን በዓል ባያከብር፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ የጌታን ቁርባን በተወሰነለት ጊዜ አላቀረበምና ያ ሰው ኃጢአቱን ይሸከማል። 14በመካከላችሁም መጻተኛ ቢኖር፥ ለጌታም የፋሲካን በዓል ቢያከብር፥ እንደ ፋሲካ ሥርዓትና እንደ ደንቡ እንዲሁ ያክብር፤ ለመጻተኛና ለአገሩ ተወላጅ አንድ ዓይነት ሥርዓት ይኑራችሁ።”
ደመናውና እሳቱ
15ማደሪያውም በተተከለ ቀን ደመናው ማደሪያውን፥ የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከማታም ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ በማደሪያው ላይ ነበረ፤ እርሱም እንደ እሳት ያለ አምሳል ነበረ። 16ሁልጊዜ በማደርያው ላይ እንዲሁ ነበረ፤ በቀን ደመና በሌሊትም የእሳት አምሳል ይሸፍነው ነበር። 17ደመናውም ከድንኳኑ ላይ በማናቸውም ጊዜ ሲነሣ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም ባረፈበት ስፍራ በዚያ የእስራኤል ልጆች ይሰፍሩ ነበር። 18በጌታ ትእዛዝ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፥ በጌታም ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፤ ደመናው በማደሪያው ላይ ባረፈበት ጊዜያት ሁሉ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር። 19ደመናውም በማደሪያው ላይ ለብዙ ቀኖች በቈየም ጊዜ እንኳ የእስራኤል ልጆች የጌታን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር። 20አንዳንድ ጊዜ ደመናው ለጥቂት ቀኖች በማደሪያው ላይ ይቈይ ነበር፤ በዚያ ጊዜ እንደ ጌታ ትእዛዝ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፤ እንደ ጌታም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር። 21አንዳንድ ጊዜም ደመናው ከማታ ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ ይቈይ ነበር፤ በጥዋትም ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዛሉ፥ ወይም ባለማቋረጥ ቀኑንም ሌሊቱንም የሚቈይ ቢሆን፥ ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። 22ደመናውም ሁለት ቀን ወይም አንድ ወር ወይም ረጅም ጊዜ ቆይቶ በማደሪያው ላይ ቢቀመጥ የእስራኤል ልጆች በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር፤ ነገር ግን በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። 23በጌታ ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፥ በጌታም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር፥ ጌታ በሙሴ አንደበት እንዳዘዘ የጌታን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ