ኦሪት ዘኍልቊ 8:1-14

ኦሪት ዘኍልቊ 8:1-14 መቅካእኤ

ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለአሮን ንገረው እንዲህም በለው መብራቶቹን ስትለኩስ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ያበራሉ።” አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው በመቅረዙ ፊት መብራቶቹን ለኰሰ። መቅረዙም እንዲህ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ተሠራ፤ ከእግሩ እስከ አበቦቹ ድረስ ሥራው ተቀጥቅጦ የተሠራ ነበረ፤ ጌታ ሙሴን እንዳሳየው ምሳሌ መቅረዙን እንዲሁ አድርጎ ሠራው። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው። እነርሱንም ለማንጻት እንዲህ ታደርግላቸዋለህ፤ ኃጢአትን የሚያነጻውን ውኃ እርጫቸው፥ በገላቸውም ላይ ያለውን ጠጉር ሁሉ በምላጭ ይላጩ፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፥ ራሳቸውንም ንጹሕ ያድርጉ። ወይፈንን፥ ለእህሉም ቁርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄትን ይውሰዱ፥ ሌላውንም ወይፈን ለኃጢአት መሥዋዕት ውሰድ። ሌዋውያንንም በመገናኛው ድንኳን ፊት አቅርብ፤ የእስራኤልንም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስብ። ሌዋውያንንም በጌታ ፊት ባቀረብካቸው ጊዜ የእስራኤል ልጆች በሌዋውያን ላይ እጃቸውን ይጫኑባቸው። አሮንም ሌዋውያን ጌታን እንዲያገለግሉ ከእስራኤል ልጆች መካከል ለመወዝወዝ ቁርባን ሌዋውያንን በጌታ ፊት ያቅርብ። ሌዋውያኑም በወይፈኖቹ ራሶች ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ፤ ለሌዋውያንም ማስተስረያ እንዲሆኑ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ለጌታ አቅርብ። ሌዋውያንንም በአሮንና በልጆቹ ፊት ታቆማቸዋለህ፥ በጌታም ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ታቀርባቸዋለህ። እንዲሁ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ትለያለህ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሆናሉ።