ኦሪት ዘኍልቊ 5
5
የረከሰ ሰው
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“የእስራኤል ልጆች የለምጽ ደዌ ያለበትን ሁሉ፥ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ፥ ሬሳንም በመንካት የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው፤ 3ወንዱንና ሴቱን አውጡ፤ እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈሩ አወጡአቸው።” 4የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ እነርሱንም ከሰፈሩ አወጡአቸው፤ ጌታ ሙሴን እንደ ተናገረው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ።
ኑዛዜ እና ካሣ
5 #
ዘሌ. 6፥1-7። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 6“ለእስራኤል ልጆች ተናገር፦ ወንድ ወይም ሴት በጌታ ላይ ፈጽሞ እምነት በማጉደል ሰው የሚሠራውን ማናቸውንም ኃጢአት ቢሠሩ፥ የሠራው ያ ሰው በደለኛ ነው፥ 7የሠራውንም ኃጢአት ይናዘዝ፤ የወሰደውንም በሙሉ ይመልስ፥ በእርሱም ላይ አምስት እጅ ይጨምርበት፥ ለበደለውም ሰው ይስጠው። 8ነገር ግን በዳዩ ይመልስለት ዘንድ ለተበዳዩ ሰውዮ ዘመድ ባይኖረው፥ ስለ በደል ለጌታ የሚመልሰው ነገር ለካህኑ ይሆናል፥ ይህም ስለ እርሱ ማስተስረያ ከሚደረግበት የማስተስረያ አውራ በግ ላይ ይጨመር። 9የእስራኤልም ልጆች ለካህኑ የሚያቀርቡትን ማናቸውም የተቀደሱ ነገሮች ስጦታ ሁሉ ለእርሱ ይሆናሉ። 10የማናቸውም ሰው የተቀደሱ ነገረሮች ለራሱ ለሰውዬው ይሆናሉ፤ ማናቸውም ሰው ለካህኑ የሚሰጠው ሁሉ ግን ለካህኑ ይሆናል።”
ታማኝ ስላልሆነች ሚስት
11ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 12“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ የማንኛውም ሰው ሚስት እርሱን ትታ ፈቀቅ ብትል፥ ለእርሱም ፍጹም ታማኝ ባትሆን፥ 13ከሌላም ሰው ጋር ብትተኛ፥ ከባልዋም ዐይን ቢሸሸግ፥ እርሷም ተሰውራ ብትረክስ፥ ምስክርም ባይኖርባት፥ በምንዝርም ባትገኝ፥ 14በባልዋም ላይ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ እርሷም በመርከስዋ ስለ ሚስቱ ቢቀና፤ ወይም እርሷ ሳትረክስ በእርሱ ላይ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፤ 15ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፥ የኢፍ መስፈሪያም አሥረኛ እጅ የገብስ ዱቄት የሆነውን ስለ እርሷ የሚቀርበውን ቁርባን ያምጣ፤ የቅንዓት የእህል ቁርባን ነውና፥ በደልንም የሚያስታውስ የመታሰቢያ የእህል ቁርባን ነውና ዘይት አያፍስስበት፥ ዕጣንም አይጨምርበት።
16“ካህኑም ያቀርባታል በጌታም ፊት ያቆማታል፤ 17ካህኑም የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ዕቃ ይወስዳል፤ ካህኑም በማደሪያው ደጃፍ ካለው ትቢያ ወስዶ በውኃው ውስጥ ይጨምረዋል፤ 18ካህኑም ሴቲቱን በጌታ ፊት ያቆማታል፥ የሴቲቱንም የተሠራ ጠጉር ይፈታል፥ በእጅዋም የመታሰቢያ የእህል ቁርባን የሆነውን የቅንዓት የእህል ቁርባን ያኖራል፤ ካህኑም እርግማንን የሚያመጣውን መራራ ውኃ በእጁ ይይዛል። 19ሴቲቱንም እንዲህ ብሎ ካህኑ ያምላታል፦ ‘ከአንቺ ጋር ሌላ ወንድ ካልተኛ፥ በባልሽም ሥልጣን ሥር እየነበርሽ ራስሽን ለማርከስ ዘወር ካላልሽ፥ እርግማንን ከሚያመጣው ከዚህ መራራ ውኃ የተጠበቅሽ ሁኚ፤ 20ነገር ግን በባልሽም ሥልጣን ሥር እያለሽ እርሱን ትተሽ ፈቀቅ በማለት ራስሽን ያረከስሽ እንደሆነ፥ ከባልሽም ሌላ ከወንድ ጋር ተኝተሽ እንደሆነ፤’ 21ካህኑም ሴቲቱን በመርገም መሐላ ያምላታል፥ ካህኑም ሴቲቱን እንዲህ ይላታል፦ ‘ጌታ ጭንሽን እያመነመነ ሆድሽንም እየነፋ፥ በሕዝብሽ መካከል ጌታ ለመርገምና ለመሐላ የምትሆኚ ያድርግሽ፤ 22እርግማንንም የሚያመጣው ይህ ውኃ ወደ ሆድሽ ይግባ፥ ሆድሽንም ይንፋው፥ ጭንሽንም ያሰልስለው፤’ ሴቲቱም፦ ‘አሜን አሜን’ ትላለች።
23“ካህኑም እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ላይ ይጽፋቸዋል፥ በመራራውም ውኃ ያጠፋቸዋል፤ 24እርግማን የሚያመጣውንም መራራ ውኃ ለሴቲቱ ያጠጣታል፤ የእርግማኑም ውኃ በገባባት ጊዜ መራራ የሆነ ሥቃይ ያመጣባታል። 25ካህኑም የቅንዓቱን የእህል ቁርባን ከሴቲቱ እጅ ይወስዳል፥ የእህሉንም ቁርባን በጌታ ፊት ይወዘውዘዋል፥ ወደ መሠዊያውም ያመጣዋል፤ 26ካህኑም ከእህሉ ቁርባን አንድ እፍኝ ሙሉ ለመታሰቢያው ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፥ ከዚያም በኋላ ሴቲቱ ውኃውን እንድትጠጣ ያደርጋታል። 27ውኃውንም እንድትጠጣ ካደረጋት በኋላ እንዲህ ትሆናለች፤ የረከሰች ብትሆንና ለባልዋ ፍጹም ታማኝ ባትሆን፥ እርግማንን የሚያመጣው ውኃ ገብቶ መራራ ሥቃይ ያመጣባታል፥ ሆድዋም ይነፋል፥ ጭንዋም ይሰለስላል፤ ሴቲቱም በሕዝብዋ መካከል ለመርገም ትሆናለች። 28ይልቁንም ሴቲቱ ሳትረክስ ንጹሕ ብትሆን ከእርግማን የተጠበቀች ትሆናለች፥ ልጅንም መፀነስ ትችላች።
29“ሚስት በባልዋ ሥልጣን ሥር እያለች እርሱን ትታ ፈቀቅ በማለት ራስዋን በምታረክስ ጊዜ ያለው የቅንዓት ሕግ ይህ ነው፤ 30ወይም በባልዋ ላይ የቅንዓት መንፈስ መጥቶበት ስለ ሚስቱ በሚቀና ጊዜ ቅንዓትን በሚመለከት ሕጉ ይህ ነው፤ ሴቲቱንም በጌታ ፊት ያቁማት፥ ካህኑም ይህን ሕግ ሁሉ በእርሷ ላይ ይፈጽምባት። 31ሰውዮውም ከበደል ንጹሕ ይሆናል፥ ሴቲቱም በደልዋን ትሸከማለች።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቊ 5: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ