ኦሪት ዘኍልቊ 32:20-42

ኦሪት ዘኍልቊ 32:20-42 መቅካእኤ

ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህንስ ነገር ብታደርጉ፥ ተዘጋጅታችሁም በጌታ ፊት ወደ ጦርነት ብትሄዱ፥ እርሱም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያሳድድ ድረስ ከእናንተ ለጦርነት የተዘጋጀው ሰው ሁሉ በጌታ ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥ ምድሪቱ በጌታ ፊት ድል ትሆናለች፤ ከዚያ በኋላ ትመለሳላችሁ፥ በጌታም ፊት በእስራኤል ዘንድ ከግዳጃችሁ ነጻ ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በጌታ ፊት ርስት ትሆንላችኋለች። እናንተ ግን እንዲህ ባታደርጉ፥ እነሆ፥ በጌታ ላይ ኃጢአትን ሠርታችኋል፤ ኃጢአታችሁም በእውነት እንደሚያገኛችሁ እወቁ። ለልጆቻችሁ ከተሞች፥ ለበጎቻችሁም በረቶች ሥሩ፤ ከአንደበታችሁም የወጣውን ቃል ፈጽሙ።” የጋድና የሮቤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ አሉት፦ “እኛ ባርያዎችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን። ልጆቻችን፥ ሚስቶቻችንም፥ መንጎቻችንም፥ እንስሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤ ዳሩ ግን እኛ ለጦርነት የተዘጋጀነው ባርያዎችህ ሁሉ በጌታ ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት ለመዋጋት እንሻገራለን።” ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን የነዌንም ልጅ ኢያሱን የእስራኤልንም ልጆች ነገድ አለቆች ስለ እነርሱ አዘዘ። ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ለጦርነት የተዘገጋጁት የጋድና የሮቤል ልጆች ሁሉ ከእናንተ ጋር በጌታ ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ። ለጦርነት ተዘጋጅተው ከእናንተ ጋር ባይሻገሩ ግን በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ።” የጋድና የሮቤልም ልጆች መልሰው እንዲህ አሉት፦ “ጌታ ለእኛ ለባርያዎችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን። ለጦርነት ተዘጋጅተን በጌታ ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፥ ከዮርዳኖስም ማዶ ከወዲሁ የወረስነው ርስት ይሆንልናል።” ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ግዛት፥ ምድሪቱንና ከተሞቹን በከተሞቹም ዙሪያ ያሉትን ግዛቶች ሰጣቸው። የጋድም ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን ሠሩ፤ እንዲሁም ዓጥሮትሽፋንን፥ ኢያዜርን፥ ዮግብሃን፥ ቤትነምራን፥ ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ። የሮቤልም ልጆች የሠሩአቸው ሐሴቦንን፥ ኤልያሊን፥ ቂርያትይምን፥ ስማቸውም የተለወጠውን ናባውን፥ በኣልሜዎንን፥ ሴባማን ነበር፤ እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በሌላ ስም ጠሩአቸው። የምናሴም ልጅ የማኪር ልጆች ወደ ገለዓድ ሄዱ፥ ያዝዋትም፥ በእርሷም የነበሩትን አሞራውያንን አሳደዱ። ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠ፤ እርሱም በእርሷ ተቀመጠ። የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮቻቸውን ያዘ፥ እነርሱንም የኢያዕር መንደሮች ብሎ ጠራቸው። ኖባህም ሄደ ቄናትንም መንደሮቻቸውንም ያዘ፥ እነርሱንም በስሙ ኖባህ ብሎ ጠራቸው።