የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 32

32
የዮርዳኖስን ማዶ መያዝና መከፋፈል
1የሮቤልና የጋድ ልጆችም እጅግ ብዙ እንስሶች ነበሩአቸው፤ እነሆም፥ የኢያዜር ምድርና የገለዓድ ምድር ለእንስሶች የተመቸ ስፍራ እንደ ነበረ ባዩ ጊዜ፥ 2የጋድና የሮቤል ልጆች መጥተው ሙሴንና ካህኑን አልዓዛርን የማኅበሩንም አለቆች እንዲህ አሉአቸው፦ 3“ዓጣሮት፥ ዲቦን፥ ኢያዜር፥ ነምራ፥ ሐሴቦን፥ ኤልያሊ፥ ሴባማ፥ ናባው፥ ባያን፥ 4ጌታ የእስራኤል ማኅበር እንዲወርሰው ያደረገው ምድር ሲሆን፥ ለእንስሶች የተመቸ ምድር ነው፤ ለእኛም ለባርያዎችህ እንስሶች አሉን።” 5እነርሱም በመቀጠል እንዲህ አሉ፦ “እኛስ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝተን እንደሆነ ይህን ምድር ለባርያዎችህ ርስት አድርገህ ስጠን፤ ወደ ዮርዳኖስም ማዶ አታሻግረን።”
6ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ በዚህ ትቀመጣላችሁን? 7ጌታ ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ የእስራኤልን ልጆች ልብ ለምን ታደክማላችሁ? 8#ዘኍ. 13፥17-33።ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ እንዲህ አደረጉ። 9ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ ሄደው ምድሪቱን ባዩ ጊዜ፥ ጌታ ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ የእስራኤልን ልጆች ልብ አደከሙ። 10#ዘኍ. 14፥26-35።በዚያም ቀን የጌታ ቁጣ ነደደ እንዲህም ብሎ ማለ፦ 11‘ከግብጽ የወጡት ዕድሜአቸው ሀያ ዓመት የሞላቸውና ከዚያም በላይ ያሉት ሰዎች እኔን ፈጽመው አልተከተሉምና ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ለመስጠት የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ 12ዳሩ ግን ለዮፎኔ ልጅ ካሌብና ለነዌ ልጅ ለኢያሱ በእውነት ጌታን ፈጽመው ስለ ተከተሉ ይህ እንዲህ አይሆንም።’ 13የጌታም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በጌታም ፊት ክፉ ያደረገ ትውልድ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ ውስጥ አቅበዘበዛቸው። 14እነሆም፥ የጌታን መዓት በእስራኤል ላይ አብዝታችሁ ለመጨመር እናንተ የኃጢአተኞች ትውልድ በአባቶቻችሁ ፋንታ ተነሣችሁ! 15እርሱን ከመከተል ብትመለሱ እርሱ ዳግመኛ ሕዝቡን በምድረ በዳ ይተዋል፤ ይህንንም ሕዝብ ሁሉ ታጠፋላችሁ።”
16ወደ እርሱም ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “በዚህ ለበጎቻችን በረቶች ለልጆቻችንም ከተሞች እንሠራለን፤ 17እኛ ግን ለጦርነት ተዘጋጅተን ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ በእስራኤል ልጆች ፊት እንድሄዳለን፤ በዚህም ምድር ስላሉ ሰዎች ልጆቻችን በተመሸጉ ከተሞች ይቀመጣሉ። 18የእስራኤል ልጆች ሁሉ ርስታቸውን እስኪወርሱ ድረስ ወደ ቤቶቻችን አንመለስም፤ 19ከዮርዳኖስ ወዲህ ወደ ምሥራቅ ርስታችን ደርሶናልና እኛ ከዮርዳኖስ ማዶ ከእርሱም ወደዚያ ያለውን ከእነርሱ ጋር ርስት አንወርስም።”
20ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህንስ ነገር ብታደርጉ፥ ተዘጋጅታችሁም በጌታ ፊት ወደ ጦርነት ብትሄዱ፥ 21እርሱም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያሳድድ ድረስ ከእናንተ ለጦርነት የተዘጋጀው ሰው ሁሉ በጌታ ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥ 22ምድሪቱ በጌታ ፊት ድል ትሆናለች፤ ከዚያ በኋላ ትመለሳላችሁ፥ በጌታም ፊት በእስራኤል ዘንድ ከግዳጃችሁ ነጻ ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በጌታ ፊት ርስት ትሆንላችኋለች። 23እናንተ ግን እንዲህ ባታደርጉ፥ እነሆ፥ በጌታ ላይ ኃጢአትን ሠርታችኋል፤ ኃጢአታችሁም በእውነት እንደሚያገኛችሁ እወቁ። 24ለልጆቻችሁ ከተሞች፥ ለበጎቻችሁም በረቶች ሥሩ፤ ከአንደበታችሁም የወጣውን ቃል ፈጽሙ።”
25የጋድና የሮቤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ አሉት፦ “እኛ ባርያዎችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን። 26ልጆቻችን፥ ሚስቶቻችንም፥ መንጎቻችንም፥ እንስሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤ 27ዳሩ ግን እኛ ለጦርነት የተዘጋጀነው ባርያዎችህ ሁሉ በጌታ ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት ለመዋጋት እንሻገራለን።”
28 # ኢያ. 1፥12-15። ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን የነዌንም ልጅ ኢያሱን የእስራኤልንም ልጆች ነገድ አለቆች ስለ እነርሱ አዘዘ። 29ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ለጦርነት የተዘገጋጁት የጋድና የሮቤል ልጆች ሁሉ ከእናንተ ጋር በጌታ ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ። 30ለጦርነት ተዘጋጅተው ከእናንተ ጋር ባይሻገሩ ግን በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ።” 31የጋድና የሮቤልም ልጆች መልሰው እንዲህ አሉት፦ “ጌታ ለእኛ ለባርያዎችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን። 32ለጦርነት ተዘጋጅተን በጌታ ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፥ ከዮርዳኖስም ማዶ ከወዲሁ የወረስነው ርስት ይሆንልናል።”
33ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ግዛት፥ ምድሪቱንና ከተሞቹን በከተሞቹም ዙሪያ ያሉትን ግዛቶች ሰጣቸው። 34የጋድም ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን ሠሩ፤ 35እንዲሁም ዓጥሮትሽፋንን፥ ኢያዜርን፥ ዮግብሃን፥ 36ቤትነምራን፥ ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ። 37የሮቤልም ልጆች የሠሩአቸው ሐሴቦንን፥ ኤልያሊን፥ ቂርያትይምን፥ 38ስማቸውም የተለወጠውን ናባውን፥ በኣልሜዎንን፥ ሴባማን ነበር፤ እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በሌላ ስም ጠሩአቸው። 39የምናሴም ልጅ የማኪር ልጆች ወደ ገለዓድ ሄዱ፥ ያዝዋትም፥ በእርሷም የነበሩትን አሞራውያንን አሳደዱ። 40ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠ፤ እርሱም በእርሷ ተቀመጠ። 41የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮቻቸውን ያዘ፥ እነርሱንም የኢያዕር መንደሮች ብሎ ጠራቸው። 42ኖባህም ሄደ ቄናትንም መንደሮቻቸውንም ያዘ፥ እነርሱንም በስሙ ኖባህ ብሎ ጠራቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ