የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 14

14
ሕዝቡ ማመፁ
1ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ፤ በዚያም ሌሊት ሕዝቡ አለቀሰ። 2የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አሉአቸው፦ “በግብጽ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! ወይም በዚህ ምድረ በዳ ምነው በሞትን ኖሮ! 3ጌታም በሰይፍ እንድንሞት ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሚስቶቻችንና ልጆቻችን ለምርኮ ይሆናሉ፤ ወደ ግብጽ መመለስ አይሻለንምን?”
4እርስ በርሳቸውም፦ “ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብጽ እንመለስ” ተባባሉ። 5ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ማኅበር በሆነው ጉባኤ ሁሉ ፊት በግምባራቸው ወድቀው ሰገዱ። 6ምድርን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ፦ “ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም የሆነች ናት። 8ጌታስ በእኛ ደስ የሚሰኝ ቢሆን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርሷንም ይሰጠናል። 9#ዕብ. 3፥16።ብቻ፥ በጌታ ላይ አታምፁ፤ ለእኛ እንደ እንጀራ ቁራሽ ናቸውና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ ጌታም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው።” 10ማኅበሩ ሁሉ ግን በድንጋይ ሊወግሯቸው ተማከሩ። የጌታም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ተገለጠ።
11ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በመካከላቸውም ስላደረግሁት ተአምራት ሁሉ እንኳ እስከ መቼ ድረስ በእኔ አያምኑም? 12ከርስታቸው እነርሱን ለማጥፋት በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ አንተንም ከእነርሱ ይልቅ ታላቅና ኃያል የሆነ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”
ሙሴ ለሕዝቡ ማማለዱ
13 # ዘፀ. 32፥11-14። ሙሴ ግን ጌታን እንዲህ አለው፦ “ግብፃውያን ይሰማሉ፤ ይህን ሕዝብ ከመካከላቸው በኃይልህ አውጥተኸዋልና፤ 14ለዚችም ምድር ሰዎች ይናገራሉ። አቤቱ፥ አንተ በዚህ ሕዝብ መካከል እንደሆንህ ሰምተዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ፊት ለፊት ተገልጠሃል፥ ደመናህም በላያቸው ቆሞአል፥ በቀንም በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ በፊታቸው ትሄዳለህ። 15ይህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ዝናህን የሰሙ አሕዛብ እንዲህ ይላሉ፦ 16‘ጌታ ይህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ሊያገባቸው አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው።’ 17አሁንም፥ እባክህ፥ የጌታ ኃይል ታላቅ ይሁን፤ አንተም እንዲሁ ቃል ኪዳን ያደረግከው እንዲህ ብለህ በተነናገርህ ጊዜ ነው፦ 18#ዘፀ. 20፥5፤6፤ 34፥6፤7፤ ዘዳ. 5፥9፤10፤ 7፥9፤10።‘ጌታ ታጋሽና ጽኑ ፍቅሩ የበዛ፥ በደልንና መተላለፍን ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን በደል እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው።’ 19ይህን ሕዝብ ከግብጽ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልከው፥ እባክህ፥ እንደ ጽኑ ፍቅርህ ብዛት የዚህን ሕዝብ በደል ይቅር በል።”
20ጌታም እንዲህ አለ፦ “እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤ 21#ዕብ. 3፥18።ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝና በእውነት የጌታ ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል። 22በግብጽ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ክብሬንና ተአምራቴን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ዐሥር ጊዜ እኔን ስለ ተፈታተኑኝ፥ ድምፄንም ስላልሰሙ፥ 23በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፥ እነዚህም የናቁኝ ሰዎች ሁሉ አያይዋትም፤ 24#ኢያ. 14፥9-12።ባርያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለ ተከተለኝ እርሱ ሄዶ ወደ ነበረበት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል። 25አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በሸለቆው ውስጥ ስለ ተቀመጡ ነገ ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር በኩል በሚወስደው መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።”
የመውረር ሙከራው መክሸፉ
26ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 27“የሚያጉረመርምብኝን ይህን ክፉ ማኅበር እስከ መቼ እታገሠዋለሁ? በእኔ ላይ የሚያጉረመርሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጉረምረም ሰምቻለሁ። 28እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ 29#ዕብ. 3፥17።በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ ከአጠቃላይም ቁጥራችሁ፥ በእኔ ላይ ያጉረመረሙ ዕድሜአቸው ሀያ ዓመት የሆናቸውና ከዚያም በላይ ሆነው የተቈጠሩት ሁሉ፥ 30ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርሷ ላስቀምጣችሁ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም። 31ነገር ግን ምርኮኛ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን ወደ ምድሪቱ አስገባቸዋለሁ፥ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቋታል። 32እናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ። 33#የሐዋ. 7፥36።ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት እረኛች ይሆናሉ፥ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ዝሙታችሁን ይሸከማሉ። 34ምድሪቱን በሰላለችሁባት ቀን ቍጥር፥ አርባ ቀን፥ እያንዳንዱም ቀን እንደ አንድ ዓመት ሆኖ፥ በደላችሁን አርባ ዓመት ትሸከማላችሁ፥ መከፋቴንም ታውቃላችሁ።’ 35እኔ ጌታ፦ በእኔ ላይ በተሰበሰበ በዚህ ክፉ ማኅበር ሁሉ ላይ በእውነት እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ተናገርሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ ያልቃሉ፥ በዚያም ይሞታሉ።”
36ምድሪቱንም እንዲሰልሉ ሙሴ የላካቸው ሰዎች፥ እነርሱም ተመልሰው ስለ ምድሪቱ ክፉ ወሬ በማውራት በእርሱ ላይ ማኅበሩ ሁሉ እንዲያጉረመርሙ ያደረጉ፥ 37እነዚያ ክፉ ወሬ ስለ ምድሪቱ ያወሩ ሰዎች በጌታ ፊት በመቅሠፍት ሞቱ። 38ነገር ግን ምድሪቱን ለመሰለል ከሄዱት ከእነዚያ ሰዎች ውስጥ በሕይወት የቀሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ነበሩ።
39ሙሴም እነዚህን ቃላት ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገረ፥ ሕዝቡም እጅግ አዘኑ። 40በማግስቱም ማልደው ተነሡ፥ ወደ ተራራውም ራስ እንዲህ እያሉ ወጡ፦ እነሆ፥ እኛ በዚህ አለን፤ እኛ ኃጢአትን ሠርተናልና ጌታ ወዳለው ስፍራ እንወጣለን። 41ሙሴም እንዲህ አለ፦ “የጌታን ትእዛዝ ለምን አሁንም ትተላለፋላችሁ? ይህ አይሳካላችሁም። 42ጌታ በእናንተ መካከል አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትሸነፉ አትውጡ። 43በዚያም አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ ጌታን ከመከተል ተመልሳችኋልና ጌታ ከእናንተ ጋር አይሆንም።” 44የጌታ ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ ወጥተው ባይጓዙም እንኳ እነርሱ ግን ወደ ተራራው ራስ ለመውጣት ደፈሩ። 45በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ አማሌቃውያንና ከነዓናውያን ወረዱ፥ አሸንፈወዋቸውም እስከ ሔርማ ድረስ አሳደዱአቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}