የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 8:13-38

የማርቆስ ወንጌል 8:13-38 መቅካእኤ

ከዚያም ትቷቸው በጀልባ ወደ ማዶ ተሻገረ። ደቀመዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለረሱ፥ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። ኢየሱስም፥ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው፥ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት ምን ያነጋግራችኋል? አሁንም አታስተውሉምን? ልብ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” እነርሱም፥ “ዐሥራ ሁለት” አሉት። “ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺህ በቆረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሰባት” አሉት። እርሱም፥ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን” አላቸው። ከዚያም ወደ ቤተሳይዳ መጡ፤ ጥቂት ሰዎችም አንድ ዐይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ለመኑት። እርሱም የዐይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከሰፈር ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎበት፥ እጁንም በላዩ ጭኖ፥ “ምን የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፥ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ። ኢየሱስም እንደገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ። ከዚያም፥ “ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አትናገር” ብሎ ወደ ቤቱ ላከው። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፈልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፥ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። ቀጥሎም፥ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው። ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፥ በሽማግሌዎች፥ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፥ እንደሚገደል፥ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፥ “አንተ ሰይጣን፥ ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው። ከዚህ በኋላ፥ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ነፍሱን ለማዳን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ለመሆኑ፥ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፥ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሲመጣ ያፍርበታል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች

Free Reading Plans and Devotionals related to የማርቆስ ወንጌል 8:13-38