የማርቆስ ወንጌል 4:30-41

የማርቆስ ወንጌል 4:30-41 መቅካእኤ

እርሱም እንዲህ አለ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፤ እርሷም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች፤ ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፤ የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታወጣለች።” መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፤ ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀመዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር። በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ “ወደ ማዶ እንሻገር፤” አላቸው። ሕዝቡንም ትተው በታንኳዪቱ ውስጥ እንዳለ ወሰዱት፤ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ። ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውሃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ ቀስቅሰውትም “መምህር ሆይ! ስንጠፋ አይገድህምን?” አሉት። ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም “ዝም በል፤ ፀጥ በል፤” አለው። ነፋሱም ተወ፤ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። “እንዲህ የምትፈሩት ስለምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም?” አላቸው። እጅግም ፈሩና “እንዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች