የማርቆስ ወንጌል 13
13
ኢየሱስ ስለ ቤተ መቅደስ መፍረስና ስለ ዓለም መጨረሻ እንደ ተናገረ
(ማቴ. 24፥1-14፤ ሉቃ. 21፥5-19)
1ከቤተ መቅደስ ሲመጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ “መምህር ሆይ፤ ድንጋዮቹ እንዴት እንደ ሆኑ፥ ሕንጻውም እንዴት ውብ እንደሆነ እይ” አለው። 2ኢየሱስም መልሶ፥ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? አንዱ ድንጋይ በሌላው ላይ እንደሆነ አይቀርም፤ ሁሉም ፈራሽ ነው” አለው።
3ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ትይዩ፥ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብ፥ ዮሐንስና እንድርያስ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ 4“ይህ መቼ እንደሚሆን ንገረን፤ የዚህስ ሁሉ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድነው?” 5ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ 6ብዙዎች፥ “እኔ እርሱ ነኝ” እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። 7ስለ ጦርነትና ስለ ጦርነት ወሬ በምትሰሙበት ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህማ መሆን አለበት፤ ፍጻሜው ግን ገና ነው። 8ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በብዙ ቦታም የመሬት መንቀጥቀጥና ራብ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
9 #
ማቴ. 10፥17-20፤ ሉቃ. 12፥11፤12። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ለሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኵራብ ይገርፏችኋል፤ ምስክር ትሆኑም ዘንድ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። 10አስቀድሞ ግን ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ መሰበክ አለበት። 11ተይዛችሁ ለፍርድ በምትቀርቡበት ጊዜ፥ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ እንጂ ምን እንናገራለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። 12ወንድም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ይገድሏቸዋልም። 13#ማቴ. 10፥22።በእኔ ምክንያት በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል።
14 #
ዳን. 9፥27፤ 11፥31፤ 12፥11፤ 1መቃ. 1፥54፤ 6፥7። የጥፋት ርኩሰት ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ 15#ሉቃ. 17፥31።በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤ 16በእርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። 17በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው 18ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ 19#ዳን. 12፥1፤ ራእ. 7፥14።በመጀመሪያ እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ፥ እንዲሁ ደግሞም ወደ ፊት አቻ የሌለው ታላቅ መከራ ይሆናልና። 20ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሯል። 21በዚያን ጊዜ ማንም፥ “እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው?” ቢላችሁ ወይም፥ “እነሆ፤ እዚያ ነው” ቢላችሁ አትመኑ። 22ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፥ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፥ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ። 23ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ።
ስለ ሰው ልጅ መምጣት
(ማቴ. 24፥29-31፤ ሉቃ. 21፥25-28)
24 #
ኢሳ. 13፥10፤ ኢዩ. 2፥10፤31፤ 3፥15፤ ራእ. 6፥12፤ ኢሳ. 13፥10፤ ሕዝ. 32፥7። በዚያን ጊዜ፥ ከመከራው በኋላ ፀሓይ ትጨልማለች፥ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ 25#ኢሳ. 34፥4፤ ራእ. 6፥13፤ ኢዩ. 2፥10።ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ። 26#ዳን. 7፥13፤ ራእ. 1፥7።በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኋይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል። 27እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፥ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል።
የበለሷ ዛፍ ምሳሌ
(ማቴ. 24፥34-35፤ ሉቃ. 21፥29-33)
28ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፥ ቅጠሏ ሲያቆጠቁጥ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤ 29እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፥ በደጅም እንደሆነ ዕወቁ። 30እውነት እላችኋለሁ፥ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤ 31ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።
ኢየሱስ የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ማንም አያውቅም
(ማቴ. 24፥36-44)
32 #
ማቴ. 24፥36። ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያችም ሰዓት ከአብ በቀር፥ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም አያውቅም። 33ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፥ ጸልዩም። 34#ሉቃ. 12፥36-38።ይህም ቤቱን ለአገልጋዮቹ ትቶ፥ እያንዳንዱን አገልጋይ በየሥራ ድርሻው ላይ አሰማርቶ፥ በረኛው ነቅቶ እንዲጠብቅ አዝዞ የሄደውን ሰው ይመስላል። 35እንግዲህ የቤቱ ባለቤት በምሽት ወይም በውድቅት፥ በዶሮ ጩኸት ወይም ጎሕ ሲቀድ እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤ 36ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ 37ለእናንተ የምነግራችሁን ለሰው ሁሉ እናገራለሁ፤ ተግታችሁ ጠብቁ።
Currently Selected:
የማርቆስ ወንጌል 13: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ