የማርቆስ ወንጌል 12
12
ስለ ወይን አትክልቱ ሠራተኞች ምሳሌ
(ማቴ. 21፥33-46፤ ሉቃ. 20፥9-19)
1 #
ኢሳ. 5፥1፤2። ከዚያም እንዲህ እያለ በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው ወይን ተከለ፤ ዙሪያውን ዐጠረ፤ ለመጭመቂያው ጉድጓድ ቆፈረ፤ የመጠበቂያም ማማ ሠራለት፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 2በመከር ጊዜም ከወይኑ ፍሬ እንዲያመጣለት ከአገልጋዮቹ አንዱን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። 3እነርሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት። 4እንደገናም ሌላ አገልጋይ ላከ። እነርሱም ራሱን ፈንክተውና አዋርደው መለሱት”፤ 5አሁንም እንደገና ሌላ ላከ፤ ይህኛውንም ገደሉት፤ ከሌሎች ከብዙዎቹ መካከል አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹንም ገደሉ። 6አሁንም የሚላክ ሌላ ነበረው፤ እርሱም የሚወደው ልጁ ነበረ፤ “ልጄንስ ያከብሩታል” በማለት ከሁሉ በኋላ ላከው። 7ገበሬዎቹ ግን እርስ በርሳቸው፥ ይህማ ዋናው ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለው፤ ርስቱ የእኛ ይሆናል፥ ተባባሉ፤ 8ከዚያም ይዘው ገደሉት፤ ከወይኑ ስፍራም አውጥተው ጣሉት። 9እንግዲህ የወይኑ አትክልት ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይመጣል፤ ገበሬዎቹን ይገድላል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል።
10 #
መዝ. 118፥22፤23። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ፤
የሚለውን የመጽሐፍ ቃል አላነበባችሁምን፤
11ጌታ ይህን አድርጓል፥
ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው!
12ምሳሌውን የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን ስላወቁ፥ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ስለ ፈሩ ትተውት ሄዱ።
ለቄሣር ግብር ስለ መክፈል
(ማቴ. 22፥15-22፤ ሉቃ. 20፥20-26)
13ከዚያም በነገር እንዲያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። 14እነርሱም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛ ሰው መሆንህን እናውቃለን፤ የሰዎች ማንነት ስለማይገድህም አታዳላም፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ብቻ በእውነት ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም? 15እኛስ እንክፈል ወይስ አንክፈል?” ኢየሱስ ግን ግብዝነታቸውን ዐውቆ፥ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር አምጡልኝና ልየው” አላቸው። 16እነርሱም አመጡለት፥ “ይህ የማን መልክ ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “የቄሣር ነው” አሉት። 17ኢየሱስም፥ “የቄሣርን ለቄሣር፥ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በእርሱ ተደነቁ።
ስለ ትንሣኤ ሙታን
(ማቴ. 22፥23-33፤ ሉቃ. 20፥27-40)
18 #
የሐዋ. 23፥8። ከዚህ በኋላ የሙታን ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ 19#ዘዳ. 25፥5።“መምህር ሆይ፤ የአንድ ሰው ወንድም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ ይህ ሰው ሴትዮዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል። 20ታዲያ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው አግብቷት ዘር ሳይተካ ሞተ፤ 21ሁለተኛውም ሴትዮዋን አገባት፤ እርሱም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ 22ሰባቱም አገቧት፤ ዘር ግን አልተኩም፤ በመጨረሻም ሴትዮዋ ሞተች። 23እንግዲህ፥ ሰባቱም አግብተዋታልና በትንሳኤ ለማናቸው ሚስት ልትሆን ነው?” አሉት።
24ኢየሱስም፥ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የምትስቱት እኮ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል ስለማታውቁ ነው፤ 25ሙታን ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡምም። 26#ዘፀ. 3፥6።ስለ ሙታን ግን እንደሚነሡ እግዚአብሔር
“እኔ የአብርሃም አምላክ
የይስሐቅም አምላክ
የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤”
እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቁጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? 27የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ።
ከሁሉ የምትበልጥ ትእዛዝ
(ማቴ. 22፥34-40፤ ሉቃ. 10፥25-28)
28ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፥ “ለመሆኑ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። 29#ዘዳ. 6፥4፤5።ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፥ እስራኤል ሆይ! ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ 30አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኋይልህ ውደድ።” 31#ዘሌ. 19፥18።ሁለተኛውም ይህ ነው፤ “ጐረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።” ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም። 32#ዘዳ. 4፥35።ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፥ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ 33#ሆሴዕ 6፥6።እርሱን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም አእምሮህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኋይልህ መውደድ፥ እንዲሁም ጐረቤትህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።” 34#ሉቃ. 10፥25-28።ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፥ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።
ኢየሱስ ለፈሪሳውያን ያቀረበው ጥያቄ
(ማቴ. 22፥41-46፤ ሉቃ. 20፥41-44)
35ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ? 36#መዝ. 110፥1።ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፥
ጌታ ጌታዬን፥ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች
እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው፥ ይላል።
37“ታዲያ ዳዊት ራሱ ጌታ፥ ካለው፤ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?”። ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር።
ከጸሐፍት ሥራ ስለ መጠበቅ
(ማቴ. 23፥1-36፤ ሉቃ. 20፥45-47)
38በሚያስተምርበትም ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ የተንዘረፈፈ ቀሚስ ለብሰው መዞርን ይወዳሉ፤ በየአደባባዩም የአክብሮት ሰላምታ ይሻሉ፤ 39በምኵራብ ከፍተኛውን ወንበር፥ በግብዣም ቦታ የከበሬታን ስፍራ ይፈልጋሉ፤ 40በረጅም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቁታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።”
የመበለቲቱ ስጦታ
(ሉቃ. 21፥1-4)
41ኢየሱስ በገንዘብ ማስቀመጫው አንጻር ተቀምጦ ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ገንዘብ ማስቀመጫ ሳጥን ሲያስገቡ ይመለከት ነበር። ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ አስገቡ፤ 42አንዲት ድኻ መበለትም መጥታ ሁለት ሳንቲም የሚያክል የናስ ገንዘብ ጨመረች። 43ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህቺ ድኻ መበለት ሳጥኑ ውስጥ ከጣሉት ከሌሎቹ የበለጠ አስገባች። 44እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን በድህነት ዐቅሟ ያላትን ሁሉ አውጥታ ለመኖሪያ የሚሆናትን እንዳለ ሰጠች።”
Currently Selected:
የማርቆስ ወንጌል 12: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ