የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 11

11
ጌታችን በክብር ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ገባ
(ማቴ. 21፥1-11ሉቃ. 19፥28-40ዮሐ. 12፥12-19)
1ወደ ኢየሩሳሌም በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፥ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ በማለት ላካቸው፦ 2በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፥ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈታችሁ አምጡት፤ 3ማንም፥ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” ቢላችሁ፥ “ለጌታ ያስፈልገዋል፤ በቶሎም መልሶ ይልከዋል” ብላችሁ ንገሩት። 4እነርሱም ሄዱ፤ በአንድ ቤት በራፍ እመንገድ ላይ የአህያ ውርንጫ ታስሮ አገኙት፤ ፈቱትም። 5በዚያ ከቆሙት አንዳንድ ሰዎች፥ “ውርንጫውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው። 6ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ያላቸውን ለሰዎቹ በነገሯቸው ጊዜ ፈቀዱላቸው። 7ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አምጥተው ልብሳቸውን በጀርባው ላይ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት። 8ብዙ ሰዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ለምለም የዛፍ ቅርንጫፍ እየቆረጡ ያነጥፉ ነበር። 9#መዝ. 118፥25፤26።ከፊቱ የቀደሙትና ከኋላው የተከተሉትም በታላቅ ድምፅ፤ እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ሆሣዕና! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው 10የምትመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት! ሆሣዕና በአርአያም!”
11ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም ስለመሸ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ።
ኢየሱስ የበለሷን ዛፍ እንደ ረገማት
(ማቴ. 21፥18-19)
12በማግሥቱ ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ። 13እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። 14ከዚያም ዛፏን፥ “ከአሁን ጀምሮ ለዘለዓለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ።
ኢየሱስ በቤተ መቅደስ የሚገበያዩትን እንደ አስወጣ
(ማቴ. 21፥12-17ሉቃ. 19፥45-48ዮሐ. 2፥13-22)
15ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፥ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤ 16ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ። 17#ኢሳ. 56፥7፤ ኤር. 7፥11።ሲያስተምራቸውም፥ “ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል፥ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው። 18የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፥ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና። 19በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ።
የበለሲቱ ዛፍ እንደ ደረቀች
(ማቴ. 21፥20-22)
20በማግስቱ ጠዋት በመንገድ ሲያልፉ፥ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ። 21ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምካት በለስ ደርቃለች” አለው። 22ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “በእግዚአብሔር እመኑ፤” 23#ማቴ. 17፥20፤ 1ቆሮ. 13፥2።እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ፥ “ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር” ቢለውና ይህንንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል። 24ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደ ተቀበላችሁት አድርጋችሁ ብታምኑ ይሆንላችኋል። 25#ማቴ. 6፥14፤15።እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ፥ የሰማዩ አባታችሁ ኀጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ፥ እናንተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ። 26ይቅር ባትሉ ግን የሰማዩ አባታችሁ ኀጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።
ኢየሱስ በምን ሥልጣን እንደሚሠራ የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 21፥23-27ሉቃ. 20፥1-8)
27እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚዘዋወርበት ጊዜ፥ የካህናት አለቆች፥ ጸሐፍትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀርበው፥ 28“እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን እንድታደርግስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው” አሉት። 29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እስቲ እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። 30የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ።” 31እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ከሰማይ ነው” ብንል፥ “ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?” ይለናል፤ 32“ታዲያ፥ ከሰው ነው፤ እንበልን?” ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን ያምኑ ስለ ነበር ፈሩ። 33ስለዚህ ለኢየሱስ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም፥ “እንግዲያው እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማርቆስ ወንጌል 11