ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። እንደ ጸሓፍት ሳይሆን፥ እንደ ባለ ሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ። በዚያን ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! ከኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደሆንህ ዐውቃለሁ! አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” ኢየሱስም፥ “ጸጥ በል፤ ከእርሱም ውጣ” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኃይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ወጣ። ሕዝቡ በሙሉ በመደነቅ፥ “ይህ ምንድነው? በሥልጣን ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤ ይህ አዲስ ትምህርት ምንድነው?” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ። ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ተዳረሰ። ወዲያው ከምኵራብ እንደ ወጡ፥ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገቡ። የስምዖን አማት በትኩሳት በሽታ ታማ ተኝታ ነበር፤ ስለ እርሷም ነገሩት፤ ስለዚህም እርሱ ወደ ተኛችበት በመሄድ እጇን ይዞ አስነሣት፤ ትኩሳቱም ተዋት፤ ተነሥታም ታገለግላቸው ጀመር። ጀንበር ከጠለቀች በኋላ፥ ምሽት ላይ የአካባቢው ሰዎች ሕመምተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ። የከተማዋ ሕዝብ በሙሉ በቤቱ ደጅ ላይ ተሰብስቦ ነበር። እርሱም በተለያየ በሽታ የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትም አወጣ፤ ነገር ግን አጋንንቱ የኢየሱስን ማንነት ያውቁ ስለ ነበር እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። ማለዳም ገና ጎሕ ሳይቀድ፥ ኢየሱስ ተነሥቶ ከቤት ወጣ፤ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራም ሄዶ ይጸልይ ጀመር። ስምዖንና ባልደረቦቹም ተከትለው ይፈልጉት ጀመር፤ ባገኙትም ጊዜ፥ “ሰዉ ሁሉ ይፈልግሃል” አሉት። እርሱም፥ “ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና” አላቸው። ስለዚህ ወደ ምኵራባቸው እየገባ በመስበክና አጋንንትን በማስወጣት በመላዋ ገሊላ ይዘዋወር ጀመር።
የማርቆስ ወንጌል 1 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 1:21-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች