አልፈውም ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ደረሱ፤ ወዲያው በሚቀጥለውም ሰንበት ኢየሱስ ወደ ምኲራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። ኢየሱስ፥ የሕግ መምህራን እንደሚያስተምሩት ዐይነት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ስለ ነበረ የሰሙት ሁሉ በትምህርቱ ተደነቁ። አንድ ርኩስ መንፈስ ያደረበት በምኲራባቸው የነበረ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? አንተ ማን እንደ ሆንክ እኔ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ።” ኢየሱስም ርኩሱን መንፈስ “ጸጥ ብለህ ከእርሱ ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን ጥሎ ካንፈራገጠው በኋላ በታላቅ ድምፅ እየጮኸ ከእርሱ ወጣ። “ይህ ምንድን ነው? ምን ዐይነት አዲስ ትምህርት ነው? ርኩሳን መናፍስትን እንኳ በሥልጣኑ ያዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤” እያሉ ሁሉም በመገረም እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ወዲያውኑ፥ የኢየሱስ ዝና በገሊላ ዙሪያ ባሉት አገሮች ሁሉ ተሰማ። በዚያኑ ጊዜ ኢየሱስ ከምኲራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና እንድርያስ ቤት ገባ። በቤት ውስጥ፥ የስምዖን ዐማት በንዳድ ሕመም አተኲሶአት ተኝታ ነበር፤ ስለ እርስዋም መታመም ወዲያው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም ወደ እርስዋ ቀረበና እጅዋን ይዞ አስነሣት፤ ትኲሳቱም ወዲያው ለቀቃት፤ ተነሥታም አስተናገደቻቸው። ፀሐይ ጠልቃ በመሸ ጊዜ ሰዎች በሽተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ ኢየሱስ አመጡ። የከተማው ሰዎች ሁሉ በደጅ ተሰብስበው ነበር። ኢየሱስ በልዩ ልዩ በሽታ የሚሠቃዩትን ብዙ ሰዎች ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትንም አስወጣ፤ አጋንንቱም እርሱ ማን እንደ ሆነ ያውቁ ነበር፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። ሊነጋ ሲል፥ ኢየሱስ በማለዳ ተነሥቶ ወጣና ለመጸለይ ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ሄደ፤ ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እርሱን ፍለጋ ወጥተው ሄዱ። ባገኙትም ጊዜ፥ “ሰዎች ሁሉ ይፈልጉሃል” አሉት። ኢየሱስም፦ “እኔ የመጣሁት ለማስተማር ስለ ሆነ ወንጌልን እንዳስተምር በቅርብ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ!” አላቸው። ስለዚህ በየምኲራቦቻቸው እያስተማረና አጋንንትን እያስወጣ በገሊላ ሁሉ ይዘዋወር ነበር።
የማርቆስ ወንጌል 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 1:21-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች