የማርቆስ ወንጌል 1
1
የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት
(ማቴ. 3፥1-12፤ ሉቃ. 3፥1-18፤ ዮሐ. 1፥19-28)
1የእግዚአብሔር ልጅ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ፥ 2#ሚል. 3፥1።በነቢዩ በኢሳይያስ፥ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤
“እነሆ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤
3 #
ኢሳ. 40፥3። የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤
ጥርጊያውንም አስተካክሉ
እያለ በበረሓ የሚጮኽ ድምፅ።”
4ስለዚህ መጥምቁ ዮሐንስ በበረሓ እያጠመቀና ለኃጢአት ስርየት የንስሓ ጥምቀት እየሰበከ መጣ። 5የይሁዳ አገር በሞላ፥ የኢየሩሳሌም ሰዎች በጠቅላላ ወደ እርሱ በመሄድ ኀጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቁ። 6#2ነገ. 1፥8።ዮሐንስ የግመል ጠጉር ይለብስ፥ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ፥ አንበጣና የበረሓ ማር ይበላ ነበር። 7ስብከቱም፥ “እኔ ጐንበስ ብዬ የጫማውን ማሰሪያ መፍታት ከማይገባኝ፥ ከእኔ የሚበልጥ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ 8እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል” የሚል ነበር።
የጌታችን የኢየሱስ መጠመቅ
(ማቴ. 3፥13-17፤ ሉቃ. 3፥21-22)
9በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የገሊላ ከተማ ከሆነችው ከናዝሬት መጥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። 10ከውሃው በሚወጣበትም ጊዜ፥ ሰማያት ተከፍተው፥ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ሲወርድ አየ፤ 11#ዘፍ. 22፥2፤ መዝ. 2፥7፤ ኢሳ. 42፥1፤ ማቴ. 3፥17፤ 12፥18፤ ማር. 9፥7፤ ሉቃ. 3፥22።“የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መፈተን
(ማቴ. 4፥1-11፤ ሉቃ. 4፥1-13)
12መንፈስ ቅዱስም ወዲያው ወደ በረሓ መራው፤ 13በሰይጣንም እየተፈተነ አርባ ቀን በበረሓ ቆየ። ከአራዊትም ጋር ነበር፤ መላእክትም አገለገሉት።
ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ እንደ ጀመረ
(ማቴ. 4፥14-17፤ ሉቃ. 4፥14-15)
14ዮሐንስ እስር ቤት ከገባ በኋላ፥ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ መጣ። 15#ማቴ. 3፥2።“ጊዜው ደርሶአል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ” እያለ ይሰብክ ነበር።
ኢየሱስ አራት ዓሣ አጥማጆችን እንደ ጠራ
(ማቴ. 4፥18-22፤ ሉቃ. 4፥14-15፤ 5፥1-11)
16ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፥ ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ ዓሣ አጥማጆች ስለ ነበሩ፥ መረብ ወደ ባሕር ሲጥሉ አያቸው። 17ኢየሱስም፥ “ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። 18እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። 19ትንሽ እልፍ እንዳለ፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ በጀልባ ሆነው መረባቸውን ሲያበጃጁ አያቸውና፥ 20ወዲያውኑ ጠራቸው። እነርሱም ከቅጥር ሠራተኞቹ ጋር አባታቸውን በጀልባው ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ።
ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው እንደ ዳነ
(ሉቃ. 4፥31-37)
21ከዚያም ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ፤ ኢየሱስም ወዲያው በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማር ጀመረ። 22#ማቴ. 7፥28፤29።እንደ ጸሓፍት ሳይሆን፥ እንደ ባለ ሥልጣን በማስተማሩ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ። 23በዚያን ጊዜ በምኵራባቸው ውስጥ የነበረ ርኩስ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው እንዲህ በማለት ጮኸ፤ 24“የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! ከኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደሆንህ ዐውቃለሁ! አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” 25ኢየሱስም፥ “ጸጥ በል፤ ከእርሱም ውጣ” ብሎ ገሠጸው። 26ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን በኃይል ካንፈራገጠው በኋላ እየጮኸ ወጣ። 27ሕዝቡ በሙሉ በመደነቅ፥ “ይህ ምንድነው? በሥልጣን ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፤ ይህ አዲስ ትምህርት ምንድነው?” እያሉ እርስ በርስ ተጠያየቁ። 28ወዲያውም ዝናው በገሊላ ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች ሁሉ ተዳረሰ።
ብዙ ሰዎች እንደተፈወሱ
(ማቴ. 8፥14-17፤ ሉቃ. 4፥38-41)
29ወዲያው ከምኵራብ እንደ ወጡ፥ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገቡ። 30የስምዖን አማት በትኩሳት በሽታ ታማ ተኝታ ነበር፤ ስለ እርሷም ነገሩት፤ 31ስለዚህም እርሱ ወደ ተኛችበት በመሄድ እጇን ይዞ አስነሣት፤ ትኩሳቱም ተዋት፤ ተነሥታም ታገለግላቸው ጀመር።
32ጀንበር ከጠለቀች በኋላ፥ ምሽት ላይ የአካባቢው ሰዎች ሕመምተኞችንና በአጋንንት የተያዙትን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ። 33የከተማዋ ሕዝብ በሙሉ በቤቱ ደጅ ላይ ተሰብስቦ ነበር። 34እርሱም በተለያየ በሽታ የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፤ ብዙ አጋንንትም አወጣ፤ ነገር ግን አጋንንቱ የኢየሱስን ማንነት ያውቁ ስለ ነበር እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም።
ኢየሱስ በገሊላ አውራጃዎች ዞሮ እንዳስተማረ
(ሉቃ. 4፥42-44)
35ማለዳም ገና ጎሕ ሳይቀድ፥ ኢየሱስ ተነሥቶ ከቤት ወጣ፤ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራም ሄዶ ይጸልይ ጀመር። 36ስምዖንና ባልደረቦቹም ተከትለው ይፈልጉት ጀመር፤ 37ባገኙትም ጊዜ፥ “ሰዉ ሁሉ ይፈልግሃል” አሉት። 38እርሱም፥ “ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ፤ የመጣሁት ለዚሁ ነውና” አላቸው። 39#ማቴ. 4፥23፤ 9፥35።ስለዚህ ወደ ምኵራባቸው እየገባ በመስበክና አጋንንትን በማስወጣት በመላዋ ገሊላ ይዘዋወር ጀመር።
ኢየሱስ ለምጻሙን ሰው እንዳነጻ
(ማቴ. 8፥1-4፤ ሉቃ. 5፥12-16)
40አንድ ለምጻምም ወደ እርሱ ቀርቦ ከፊቱ በመንበርከክ፥ “ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ለመነው። 41ኢየሱስም ለሰውየው በመራራት እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፥ “እፈቅዳለሁ፥ ንጻ” አለው። 42እርሱም ወዲያው ከለምጹ ነጻ፤ ከበሽታውም ተፈወሰ። 43ኢየሱስም ሰውየውን አጥብቆ በማስጠንቀቅ እንዲህ ሲል አሰናበተው፤ 44#ዘሌ. 14፥1-32።“ለማንም አንድ ነገር እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ምስክር እንዲሆናቸው ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ስለ መንጻትህም ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ” አለው። 45ሰውየው ግን በሄደበት ሁሉ ነገሩን በሰፊው አወራ፤ ወሬውንም አሠራጨ፤ በዚህ ምክንያት ኢየሱስ ወደ ማንኛውም ከተማ በግልጽ መግባት አልተቻለውም፤ ከዚህም የተነሣ ከከተማ ውጭ በሚገኙ ሰዋራ ቦታዎች መኖር ጀመረ፤ ሰዎች ግን ከየአቅጣጫው እርሱ ወዳለበት ይመጡ ነበር።
Currently Selected:
የማርቆስ ወንጌል 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ