የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሚክያስ 1

1
በሰማርያ ላይ የተላለፈ ፍርድ
1 # 2ነገ. 15፥32-38፤ 2ዜ.መ. 27፥1-7፤ 2ነገ. 16፥1-20፤ 2ዜ.መ. 28፥1-27፤ 2ነገ. 18፥1—20፥21፤ 2ዜ.መ. 29፥1—32፥33። በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታምና በአካዝ በሕዝቅያስም ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው፥ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው፥ የጌታ ቃል ይህ ነው።
2ሕዝቦች ሆይ! ሁላችሁም ስሙ፤ ምድርና ሞላዋ ታድምጥ፤ ጌታ በቅዱስ መቅደሱ ሆኖ፥ ጌታ አምላክ በእናንተ ላይ ይመስክርባችሁ።
3እነሆ፥ ጌታ ከስፍራው ይወጣልና፥ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይራመዳል።
4ተራሮች በሥሩ ይቀልጣሉ፥ ሸለቆዎችም በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፥ ከቁልቁለት እንደሚወርድ ውኃ፥ ይሰነጠቃሉ።
5ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብ በደል ምንድነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን?
6ስለዚህ ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የድንጋይ ክምር፥ ወይን እንደሚተከልበት ስፍራ አደርጋታለሁ፤ ድንጋዮችዋን ወደ ሸለቆ አፈሰዋለሁ፥ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ።
7የተቀረጹትም ምስሎችዋ ይደቅቃሉ፥ በግልሙትና ያገኘችው ዋጋ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፥ ጣዖቶችዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፤ በግልሙትና ዋጋ ሰብስባቸዋለችና፥ ወደ ግልሙትና ዋጋ ይመለሳሉ።
የይሁዳ ከተሞች ፍርድ
8በዚህ ምክንያት አለቅሳለሁ፥ ዋይ ዋይ እላለሁ፥ ባዶ እግሬንና ራቁቴን እሄዳለሁ፤ እንደ ቀበሮ አላዝናለሁ፥ እንደ ሰጎን ልጆችም የዋይታ ድምፅ አሰማለሁ።
9ቁስልዋ የማይፈወስ ነውና፤ ወደ ይሁዳ መጥቷል፥ ወደ ሕዝቤ በር ወደ ኢየሩሳሌምም ደርሶአል።
10በጋት አታውሩት፥ በፍጹም አታልቅሱ፤ በቤትልዓፍራ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ።
11በሻፊር የምትቀመጪ ሆይ፥ በራቁትነትና በእፍረት እለፊ፤ በጻኣናን የምትቀመጠው አልወጣችም፤ የቤትሐኤጼል ለቅሶ የመቆሚያ ስፍራውን ከእናንተ ይወስዳል።
12በማሮት የምትቀመጠው መልካም ነገርን ትጠባበቃለችና፤ ነገር ግን ክፉ ነገር ከጌታ እስከ ኢየሩሳሌም በር ድረስ ወርዶአል።
13በላኪሽ የምትቀመጪ ሆይ፥ ሠረገላውን ከፈረሱ ጋር አያይዢ፤ እርሷ ለጽዮን ሴት ልጆች የኃጢአት መጀመሪያ ነበረች፤ የእስራኤል በደል በአንቺ ዘንድ ተገኝቶአልና።
14ስለዚህ ለሞሬሼት ጋት የመሸኛ ስጦታዎችን ትሰጪአለሽ፤ የአክዚብ ቤቶች ለእስራኤል ነገሥታት መታለያ ይሆናሉ።
15በማሬሻ የምትቀመጪ ሆይ፥ ወራሽ አመጣብሻለሁ፤ የእስራኤል ክብር ወደ ዓዱላም ይመጣል።
16ደስ ስለምትሰኚባቸው ልጆች ራስሽን ንጪ፥ ፀጉርሽንም ተቆረጪ፤ መላጣነትሽን እንደ ንስር አስፊ፤ በምርኮ ከአንቺ ተወስደዋልና።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}