የማቴዎስ ወንጌል 9
9
ኢየሱስ ሽባውን እንደ ፈወሰ
(ማር. 2፥1-12፤ ሉቃ. 5፥17-26)
1ወደ ጀልባ ገብቶ ተሻገረና ወደ ገዛ ከተማው መጣ። 2እነሆ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ አመጡ፤ ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “ልጄ ሆይ! ጽና፤ ኃጢአቶችህ ተሰርየውልሃል፤” አለው። 3እነሆ ከጻፎች አንዳንዶቹ በልባቸው “ይህስ ይሳደባል፤” አሉ። 4ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ “ስለምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ? 5‘ኃጢአቶችህ ተሰርየውልሃል’ ከማለትና ‘ተነሣና ሂድ’ ከማለት የትኛው ይቀላል? 6ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአቶችን ሊያስተሰርይ የሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው፤” በዚያን ጊዜ ሽባውን “ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። 7ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። 8ሕዝቡም ይህንን አይተው ፈሩ፤ እንዲህ ያለውንም ሥልጣን ለሰው በመስጠቱ እግዚአብሔርን አከበሩ።
ኢየሱስ ማቴዎስን እንደ ጠራ
(ማር. 2፥13-17፤ ሉቃ. 5፥27-35)
9ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ” አለው። ተነሥቶም ተከተለው።
10 #
ሉቃ. 15፥1፤2። በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ። 11ፈሪሳውያንም ይህንን አይተው ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ለምን ይበላል?” አሉአቸው። 12ኢየሱስም ሰምቶ እንዲህ አላቸው፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ 13#ማቴ. 12፥7፤ ሆሴዕ 6፥6።ሂዱና ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤’ የሚለው ምን እንደሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና፤”
ስለ ጾም የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 2፥18-22፤ ሉቃ. 5፥33-39)
14በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ መጥተው “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ እንጾማለን፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት። 15ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ እድምተኞች ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። 16በአረጀ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ ቀዳዳውም የባሰ ይሆናል። 17በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖሩታል፤ ሁለቱም ይጠበቃሉ።”
ስለ ምኵራብ አለቃ ልጅና ደም ስለሚፈሳት ሴት
(ማር. 5፥21-43፤ ሉቃ. 8፥40-56)
18ይህንም ሲነግራቸው ሳለ እነሆ አንድ ገዢ መጥቶ እየሰገደ “ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች፤” አለው። 19ኢየሱስም ተነሥቶ ተከተለው፥ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 20እነሆ ለዐሥራ ሁለት ዓመታት ደም የሚፈስሳት ሴት ከኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ 21በልብዋ “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ፤” ብላ ታስብ ነበርና። 22ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና “ልጄ ሆይ! አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤” አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። 23ኢየሱስም ወደ ገዢው ቤት በደረሰ ጊዜ፥ አስለቃሾችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፥ 24“ልጅቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ዞር በሉ፤” አላቸው። እነርሱ ግን ሳቁበት። 25ነገር ግን ሕዝቡን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ ልጅቱም ተነሣች። 26የዚህም ወሬ ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ።
ኢየሱስ ሁለት ዐይነ ስውሮችን እንደ አዳነ
27ኢየሱስ ከዚያ አልፎ ሲሄድ ሁለት ዓይነ ስውሮች “የዳዊት ልጅ ሆይ! ማረን፤” ብለው እየጮሁ ተከተሉት። 28ወደ ቤት በገባ ጊዜ ዓይነ ስውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ኢየሱስም “ይህን ማድረግ እንደምችል ታምናላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉት። 29በዚያን ጊዜ ዐይኖቻቸውን ዳሰሰና “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው። 30ዐይኖቻቸውም ተከፈቱ። ኢየሱስም “ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ፤” ብሎ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው። 31እነርሱ ግን ሄደው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ።
ኢየሱስ አንድ ዲዳ ሰው እንደ ፈወሰ
32እየወጡ እያለ እነሆ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። 33ጋኔኑ ከወጣ በኋላ ዲዳው ተናገረ። ሕዝቡም ተደንቀው “እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ከቶ ታይቶ አይታወቅም” አሉ። 34#ማቴ. 10፥25፤ 12፥24፤ ማር. 3፥22፤ ሉቃ. 11፥15።ፈሪሳውያን ግን “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” አሉ።
35 #
ማቴ. 4፥23፤ ማር. 1፥39፤ ሉቃ. 4፥44። ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሽታንና ሕማምን ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተሞችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር። 36#ዘኍ. 27፥17፤ 1ነገ. 22፥17፤ 2ዜ.መ. 18፥16፤ ሕዝ. 34፥5፤ ማር. 6፥34።ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ አዘነላቸው፥ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተጥለው ነበርና። 37#ሉቃ. 10፥2።በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ 38እንግዲህ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ የመከሩን ጌታ ለምኑት።”
Currently Selected:
የማቴዎስ ወንጌል 9: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ