የማቴዎስ ወንጌል 4:12-22

የማቴዎስ ወንጌል 4:12-22 መቅካእኤ

ኢየሱስ ዮሐንስ እንደታሰረ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ሄደ። ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም ክልል ወደ አለችው በባሕር አጠገብ ወደምትገኝ ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ። ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ በዮርዳኖስ ማዶ ያለ፥ የባሕር መንገድ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት አገርና በሞት ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው።” ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ መስበክ ጀመረ። በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ ሳለ፥ ሁለት ወንድማማቾች፥ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ። እርሱም “ኑ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ወዲያውኑ መረባቸውን ጥለው ተከተሉት። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በታንኳ ውስጥ ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር መረባቸውን ሲጠግኑ አየና ጠራቸው። እነርሱም ወዲያውኑ ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች