ማቴዎስ 4:12-22

ማቴዎስ 4:12-22 NASV

ኢየሱስ የዮሐንስን መታሰር በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ተመለሰ። የናዝሬትንም ከተማ ትቶ፣ በዛብሎንና በንፍታሌም አካባቢ በባሕሩ አጠገብ በምትገኘው በቅፍርናሆም ከተማ ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፤ “የዛብሎን ምድር፣ የንፍታሌም ምድር፣ ከዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ አጠገብ፣ ያለው የአሕዛብ ገሊላ፣ በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ ምድር ላሉት ብርሃን ወጣላቸው።” ከዚያ ጊዜ አንሥቶ ኢየሱስ፣ “ንስሓ ግቡ፤ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና” እያለ መስበክ ጀመረ። ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ሁለት ወንድማማቾች ማለትም፣ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን አያቸው። ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕሩ ይጥሉ ነበር። ኢየሱስም፣ “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። ወዲያው መረባቸውን ትተው ተከተሉት። ዐለፍ እንዳለም፣ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች፣ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን አየ። ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋራ በጀልባ ሆነው መረባቸውን ያበጁ ነበር። ኢየሱስም ጠራቸው፤ ወዲያውኑ ጀልባቸውንም ሆነ አባታቸውን ትተው ተከተሉት።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች