የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 27:32-66

የማቴዎስ ወንጌል 27:32-66 መቅካእኤ

ሲወጡም ስምዖን የሚባል የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት። ትርጉሙ የራስ ቅል ስፍራ ወደሚባል ጎልጎታ ወደ ተባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልፈለገም። ከሰቀሉትም በኋላ ልብሶቹን ዕጣ ጥለው ተካፈሉት፤ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። የተከሰሰበትንም ምክንያት “ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ከራሱ በላይ አኖሩ። በዚያን ጊዜ ከእርሱ ጋር ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ አንዱ ደግሞ በግራው ተሰቀሉ። በዚያ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበር፤ “ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህሰ እስቲ ከመስቀል ውረድ፤” ይሉት ነበር። እንዲሁም ደግሞ ሊቃነ ካህናት፥ ከጻፎችና ከሽማግሌዎች ጋር እያፌዙ እንዲህ አሉት፦ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ነው፤ አሁን ከመስቀል ይውረድና እኛም በእርሱ እናምናለን። በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ብሏልና የሚወደው ከሆነ እስቲ አሁን ያድነው።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎችም ደግሞ እንዲህ እያሉ ይሰድቡት ነበር። ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ኢየሱስ “ኤሊ ኤሊ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም “አምላኬ አምላኬ፥ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። በዚያ ቆሙት ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ሰምተው “ኤልያስን ይጠራል” አሉ። ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠና ሰፍነግ ወስዶ የወይን ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃም አስሮ አጠጣው። የተቀሩት ግን “ተወው፤ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደሆነ እንይ” አሉ። ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኾ መንፈሱን ሰጠ። እነሆ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው ከነበሩት የብዙ ቅዱሳን በድን ተነሣ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስቷ ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አሉ። ኢየሱስን እያገለገሉት ከገሊላ የተከተሉት፥ በሩቅ ሆነው የሚመለከቱ ብዙ ሴቶች እዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያምና የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ። በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የሚባል ሀብታም ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱም የኢየሱስ ደቀመዝሙር ነበረ፤ እርሱም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ወስዶ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፤ ከዐለት በወቀረው በአዲሱ መቃብሩ አኖረው፤ በመቃብሩ በር ላይ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ። እዚያም መግደላዊት ማርያምና ሌላይቱ ማርያም በመቃብሩ ፊት ለፊት ተቀምጠው ነበር። በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ፥ ሊቃነ ካህናትና ፈሪሳውያን ከጲላጦስ ጋር ተሰበሰቡ፥ እንዲህም አሉት፦ “ጌታ ሆይ! ያ አሳች በሕይወት ሳለ ‘ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ’ እንዳለ ትዝ አለን። ስለዚህ ደቀመዛሙርቱ መጥተው እንዳይሰርቁትና ለሕዝቡም ‘ከሙታን ተነሥቶአል’ እንዳይሉ፥ መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ፤ የኋለኛው ስሕተት ከመጀመሪያው ይልቅ የከፋ ይሆናል።” ጲላጦስም “ጠባቂዎች አሉላችሁ፤ ሄዳችሁ እንደምታውቁት አስጠብቁ፤” አላቸው። ሄደውም መቃብሩን ድንጋዩን በማተም ጠባቂዎች አቆሙ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች