ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፥ ጻፎችና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህኑ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ የነገሩንም ፍጻሜ ለማየት ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። ሊቃነ ካህናትና ሸንጎው ሁሉ ሊገድሉት ፈልገው በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን አላገኙም፤ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢመጡም ምንም አላገኙም፤ በመጨረሻም ሁለት መጥተው፥ “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል፤” አሉ። ሊቀ ካህኑም ተነሥቶ “እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህኑም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ከሆንህ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥና በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህኑ ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ “ተሳድቦአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን መያዝ ለምን ያስፈልገናል? እነሆ አሁን ስድቡን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ ፊቱ ላይ ተፉበት፥ መቱት፥ በጥፊም መቱት እንዲህም አሉት “ክርስቶስ ሆይ! እስቲ ትንቢት ተናገርልን፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው?” ጴጥሮስም ከቤት ውጪ በግቢው ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድ ወደ እርሱ ቀርባ “አንተም ከገሊላዊው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው። እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቀውም” ብሎ በሁሉም ፊት ካደ። ሊወጣ ወደ በሩ ሲሄድ ሌላዪቱ አየችውና በዚያ ለነበሩት “ይህም ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ” አለቻቸው። “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ እየማለ ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዚያ ቆመው የነበሩት ጠጋ ብለው ጴጥሮስን “በእውነት አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤ አነጋገርህ ያስታውቅብሃልና” አሉት። በዚያን ጊዜ “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ ይራገምና ይምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ የተናገረውን የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።
የማቴዎስ ወንጌል 26 ያንብቡ
ያዳምጡ የማቴዎስ ወንጌል 26
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 26:57-75
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos