የማቴዎስ ወንጌል 26:47-68

የማቴዎስ ወንጌል 26:47-68 መቅካእኤ

ይህንም ገና ሲናገር ሳለ፥ እነሆ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ዱላ ይዘው ከእርሱ ጋር መጡ። አሳልፎ የሚሰጠውም “የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳመው። ኢየሱስም “ወዳጄ ሆይ! ለምን መጣህ?” አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡና እጃቸውን በኢየሱስ ላይ ጫኑ፥ ያዙትም። እነሆ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህኑን ባርያ መትቶ ጆሮውን ቆረጠው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው “ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፤ ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና። ወይስ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት አሁን ሊልክልኝ የማይችል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነ ‘እንደዚህ መሆን አለበት’ የሚሉት መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማል?” በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው “ወንበዴን እንደምትይዙ እኔን ለመያዝ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ወጣችሁን? ዕለት በዕለት በመቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው የነቢያት መጻሕፍት እንዲፈጸሙ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፥ ጻፎችና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህኑ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ የነገሩንም ፍጻሜ ለማየት ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። ሊቃነ ካህናትና ሸንጎው ሁሉ ሊገድሉት ፈልገው በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን አላገኙም፤ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢመጡም ምንም አላገኙም፤ በመጨረሻም ሁለት መጥተው፥ “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል፤” አሉ። ሊቀ ካህኑም ተነሥቶ “እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህኑም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ከሆንህ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥና በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህኑ ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ “ተሳድቦአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን መያዝ ለምን ያስፈልገናል? እነሆ አሁን ስድቡን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ ፊቱ ላይ ተፉበት፥ መቱት፥ በጥፊም መቱት እንዲህም አሉት “ክርስቶስ ሆይ! እስቲ ትንቢት ተናገርልን፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው?”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች